Get Mystery Box with random crypto!

በ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ ተሰጠ ትምህርት ሚኒስቴር የ2014ዓ.ም የ | Ethio University

በ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ ተሰጠ

ትምህርት ሚኒስቴር የ2014ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ዙሪያ ማብራሪያና መግለጫ ሰጥቷል።የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ፈተናውን በተሳካ ሁኔታ ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የገለጹ ሲሆን ሂደቱ ተማሪዎች በራስ ጥረት ብቻ ውጤታማ የሚሆኑበት ነው ብለዋል።

ከዚህም መካከል የፈተናው ዝግጅትና ህትመት በቴክኖሎጂ ታግዞ በከፍተኛ ጥንቃቄና ከደህንነት ስጋት ነፃ በሆነ መልኩ መከናወኑን በመግለጫቸው ተናግረዋል።እስከ አሁን በነበረው የቅድመ ዝግጅት ሂደትም ከሚመለከታቸው የፌደራል እና የክልል መንግስታት የስራ ሃላፊዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነም ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

በመግለጫው ሀገር አቀፍ ፈተናው በሁለት ዙር የሚሰጥ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በዚህም በመጀመሪያው ዙር የሶሻል ሳይንስ ተማሪዎች ከመስከረም 30,2015 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 02,2015 ዓ.ም ፈተናውን ሲወስዱ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከ ጥቅምት 8,2015 ዓ.ም እስከ 11,2015 ዓ.ም ፈተናውን ይወስዳሉ ተብሏል።

ተፈታኞችም ፈተናው ከሚሰጥበት ቀን በፊት ባሉት ሶስት ቀናት በሚፈተኑበት ዩኒቨርስቲዎች መገኘት እና ኦረንቴሽን መውሰድ እንደሚጠበቅባቸውም ተነግሯል።ከፈተናው ቀን በፊት ባሉት ቀናት ተማሪዎችን ወደ ፈተና ቦታ የማምጣት እና ፈተናው እንዳለቀም ተማሪዎችን ወደየመጡበት አካባቢ የመመለስ ስራ እንደሚሰራም ተገልጿል።

በተጨማሪም በመግለጫው ተፈታኞች ወደ ፈተና ቦታ ሲመጡ ይዘዋቸው እንዲመጡ የተፈቀዱ እና የተከለከሉ ቁሳቁሶች የተገለፁ ሲሆን ከነዚህም መካከል የዲጅታል ቴክኖሎጂ ውጤቶች( ስልክ፣ ላፕቶፕ፣ ፍላሽ.. ወ.ዘ.ተ)፣ ስለታማ ቁሳቁሶች እና ሌሎችም በፈተና ቦታ የተከለከሉ ቁሳቁሶች መሆናቸው ተገልጿል።

ተማሪዎች እና ወላጆች ከተሳሳቱ መረጃዎች እራሳቸውን በማራቅ ለፈተናው አሰጣጡ ስኬት የበኩላቸውን እንዲወጡም በመግለጫው ተጠይቋል።የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ከመስከረም 30,2015 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 11,2015 ዓ.ም በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ይሰጣል።