Get Mystery Box with random crypto!

ከመስከረም 2015 ዓ.ም. መጨረሻ አንስቶ በሁለት ዙር የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚ | Ethio University

ከመስከረም 2015 ዓ.ም. መጨረሻ አንስቶ በሁለት ዙር የሚሰጠውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚወስዱ አንድ ሚሊዮን ገደማ ተፈታኝ ተማሪዎች፣ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች የሚጓጓዙበትን የትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎች በመንግሥት እንደሚሸፈኑ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ለተፈታኝ ተማሪዎች የሚያስፈልጉ የምገባና መኝታ አገልግሎቶችን ለመስጠት ቁሳቁሶችን እያሟሉ መሆኑን አስታውቆ፣ ፈተናውን በዩኒቨርሲቲዎች ለማከናወን የሚያስችለውን ወጪ ለመሸፈን ተጨማሪ በጀት እንዲፈቀድለት ንግግር ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡

የ12ኛ ክፍል ፈተናን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ከነበረው ልምድ የተለየ አሠራር ለመዘርጋት ያቀደው ትምህርት ሚኒስቴር፣ ፈተናው በትምህርት ቤቶች ሳይሆን በዩኒቨርስቲዎች እንደሚሰጥ አስታውቋል፡፡ ለዚህም ሲባል ተፈታኝ ተማሪዎችን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መመደቡን የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ኃላፊ አቶ ይልቃል ወንድሜነህ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ምደባው ሲዘጋጅ በተቻለ መጠን ተማሪዎች በአቅራቢያቸው በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲመደቡ መደረጉን ያስረዱት አቶ ይልቃል፣ ‹‹በአቅራቢያቸው ያለው ዩኒቨርሲቲ በመኝታ ወይም በመፈተኛ ክፍሎች ብዛት ውስንነት ካለበት ወደ ሌላ ዞንና ክልል የመሄድ ዕድል ይኖራል፤›› ብለዋል፡፡

በተለይ ገጠር አካባቢዎች ላይ ያሉ ተማሪዎች ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ ለመጓዝ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊገጥማቸው እንደሚችል ጠቅሰው፣ አገልግሎቱ ከክልል ትምህርት ቢሮዎች ጋር በመሆን ተማሪዎቹን ወደ ዩኒቨርሲቲ እንደሚያጓጉዝ አስረድተዋል፡፡

‹ተማሪዎቹን እንዴት እናጓጉዛቸው?› የሚለው ላይ ውይይት እያደረግን ነው፡፡ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲዎች በመፈተናቸው ምክንያት ግን ወደ ተማሪዎችም ሆነ ወደ ወላጆች የሚሄድ ወጪ አይኖርም፤›› ብለዋል፡፡

ምክትል ኃላፊው፣ ተማሪዎቹ የተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ አካባቢ እንዲላመዱት ለማድረግ ሲባል ፈተናው ከሚጀመርበት ቀናት ቀደም ብለው ወደ ዩኒቨርሲቲው እንደሚጓዙ አስታውቀዋል፡፡ ወደ ዩኒቨርስቲ ሲገቡ ድምፅም ሆነ ምሥል የሚቀዳና የሚቀርፅ አሊያም ሌላ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ ይዘው መግባት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ የሚኖሩበት ከተማ ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ ተፈታኞችም ቢሆኑ በዩኒቨርስቲው ውስጥ እንዲያድሩ ለማድረግ መታቀዱንም ገልጸዋል፡፡

ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በሁለት ዙር በሚሰጠው የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከ984,000 በላይ ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀመጡ ተገልጿል፡፡ መስከረም 30 ቀን በሚጀምረው የመጀመሪያው ዙር ፈተና ለፈተና የሚቀመጡት የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ብዛታቸው 623 ሺሕ ገደማ ነው፡፡ ይህም ፈተናው የሚሰጥባቸው 42 ዩኒቨርሲቲዎች በመጀመሪያው ዙር በፈተና በአማካይ 14,827 ሺሕ ገደማ የ12ተኛ ክፍል ተማሪዎች በእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ይመደባሉ እንደማለት ነው፡፡

ይሁንና የዩኒቨርሲቲዎች ምደባ የተደረገላቸው ካላቸው ሀብትና አቅም አንፃር እየታየ መሆኑን የተናገሩት አቶ ይልቃል፣ ፈተናው በሁለት ዙር እንዲሰጥ የተወሰነው ዩኒቨርሲቲዎቹ ካላቸው አቅም አንፃር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቹ ለአንድ ዙር የተመደበላቸውን የተማሪ ብዛት ለማስተማገድ የሚጎድሏቸው ቁሳቁሶችን በመገምገም በግዥ እንዲያሟሉ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ምንጭ፡ሪፖርተር ጋዜጣ