Get Mystery Box with random crypto!

በትግራል ክልል የተቋረጠውን ትምህርት ለመጀመር በቀጣይ ሳምንት የተማሪዎች ምዝገባ ይጀመራል፦ የክል | Ethio University

በትግራል ክልል የተቋረጠውን ትምህርት ለመጀመር በቀጣይ ሳምንት የተማሪዎች ምዝገባ ይጀመራል፦ የክልሉ ትምህርት ቢሮ
******

በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጦ የነበረውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማስጀመር በቀጣይ ሳምንት በሁሉም ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባ የሚካሄድ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በትግራይ ክልል በጦርነት ምክንያት ለሦስት ዓመት ተኩል ገደማ ትምህርት ተቋርጦ መቆየቱን የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳኘው አይጠገብ ተናግረዋል።

በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሠረት አንፃራዊ ሰላም የተፈጠረ በመሆኑ በክልሉ ከሚያዝያ 18 ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባ ይጀመራል።

ትምህርት ሚኒስቴር በክልሉ ትምህርት ለማስጀመር እያደረገው ያለው መልካም ተግባር እና ጥሩ ተነሣሽነት የሚደነቅ እንደሆነ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ሚኒስቴሩ ቡድን በመላክ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ መሥራቱን ተናግረዋል።

በትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ የተመራ ቡድን መቐለ በመገኘት ትምህርት እንዲጀመር የሚያስችል ሥራ ሲሠራ መቆየቱን በማንሳት፤ በዚህም የጋራ ዕቅድ ተዘጋጅቷል ብለዋል።

በተለይ ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ በመለየት የትምህርት ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ ለማገዝ የሚያስችለውን አቅጣጫ ነድፎ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

እንደ አቶ ዳኘው ገለጻ፣ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር በክልሉ ትምህርት ለማስጀመር ሁለንተናዊ ዝግጅት ተጠናቋል።

ከቅድመ አንደኛ ክፍል (ኬጂ) እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርት የሚጀምር ሲሆን በተለያየ ምክንያት የተበታተኑ መምህራንን የማሰባሰብ ሥራ ለማከናወንም ራሱን የቻለ ወጥ ሰነድ ተዘጋጅቷል።

የነበረው የደመወዝ አለመከፈል ችግር እንዲፈታ እና ወደ ትምህርት እንዲገባም ውሳኔ ላይ መደረሱን ኢፕድ ዘግቧል።

በክልሉ ላይ የተፈጠረው ችግር ከባድ ከመሆኑ አንፃር በክልሉ ትምህርት ቢሮ ብቻ ለመፍታት ያዳግታል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሁሉም አካላት ለትግራይ ክልል እገዛ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።