Get Mystery Box with random crypto!

ላፍቅርሽ ወይ ልተው? ካወኩሽ በኋላ የደስታን ምንነት ለይቼ አውቄያለሁ ፤ ከልቤ መሳቅን በ'ውነት | ግጥም እና ወግ መድብል (poem)📜📜🔈

ላፍቅርሽ ወይ ልተው?

ካወኩሽ በኋላ
የደስታን ምንነት ለይቼ አውቄያለሁ ፤
ከልቤ መሳቅን በ'ውነት ለምጃለሁ።
የተወሳሰበው
የህይወቴ መንገድ ግልፅ ሆኖልኛል ፤
አስሮኝ የነበረው ችግሬ ተፈቷል።
ስህተት እንዳልሰራ
አገኘሁ ያልኩትን አጥፍቼ እንዳላጣው፣
የኔ ውድ ንገሪኝ
አንቺው መልሺልኝ ላፍቅርሽ ወይ ልተው?

አጠገቤ ስትሆኚ ክፋት ይርቀኛል ፤
የፍቅር ተዋጊ
የፈጣሪን መልአክ የሆንኩ ይመስለኛል።
አንቺ ስታወሪኝ
የዙርያዬ ድምፀት ፀጥታ ይሞላዋል፤
ከቃሎችሽ ውጪ
ጆሮዬ 'ሚገባ ኮሽታም ይጠፋል።
ከኔ ጋር ስትሆኚ ንፃት ይወርሰኛል፤
ራቅ ያልሽ እንደሆን ፍርሃት ያርደኛል።
የኔ ውድ ስላንቺ
ብዙ ይሰማኛል መግለጽ የማልችለው፤
እኔ እንዳልሳሳት
ራስሽ ንገሪኝ ላፍቅርሽ ወይ ልተው?

ሳቅሽን ካመጣልኝ እንደይስሀቅ መሰዋት ፣
በአብርሃም መታረድ በደስታ መሞት፣
ዳዊትን ይመስል
ለብቻዬ ሆኜ እልፍ ጦር ለመግጠም፣
አንዲት እድል መሻት በጠጠር ድል ማለም፣
ልክ እንደ አምላኬ
መስቀል ተሸክሞ ቀራንዮ መውጣት፣
ባመጣሁት መስቀል
እኔው ተቸንክሬ አንድ ህይወቴን ማጣት፣
ቀላል ይመስለኛል፤
ቅጭም እንኳን ሳልል ባደርገው ያምረኛል።
እስኪ መልሺልኝ፣
እንዲህ ከተሰማኝ ፣
ልብና አንጎል ላንቺ ይሄን ካለው፣
ውዴ ምን ተሻለኝ ላፍቅርሽ ወይ ልተው?

ባንቺ ስም ብጠ'ራ የኔን ስም ብሰጥሽ፣
በኮከብ አይነቶች
በአስደናቂ ስሞች ባዲስ ብሰይምሽ፣
የኔ ውድ ስልሽ ፍርሃት ባይኖረኝ፣
የኔ ፍቅር ስልሽ ያዝ ባያደርገኝ፣
ልቤን ከገላዬ
ለይቼ አውጥቼ ካንቺ ውስጥ ባኖረው፣
እኔ ተቀብሬ
ልቤ ከልብሽ ጋር አንድ ምት ቢኖረው፣
የትም ቦታ ብሆን በደስታ እሞላለው፤
ታዲያ ምን ትያለሽ ላፍቅርሽ ወይ ልተው?

ለኔ ህይወት አልባው እስትንፋስ መሆንሽን፣
ጨለማ ውስጥ ለኖርኩ ብርሃን ማብራትሽን፣
ተጠምቼ ስኖር
ፍቅርን የተሞላ እንስራ ማምጣትሽን፣
በልቤ ክፍተት ውስጥ
የማይነቃነቅ ቀስት ማኖርሽን፣
አንዱንም ሳልነግርሽ ሁሉንም ሳታውቂው፣
ባጣሽ ስለማልችል
በቅድሚያ ንገሪኝ ላፍቅርሽ ወይ ልተው?

CanCazım

@ethiopianpoem1
@yoyo556