Get Mystery Box with random crypto!

የልብ ነገር ክፍል ሰባት (ፉአድ ሙና) *** አመመኝ አልልም አልተነካም ጅስሜ፣ ጤነኛ አልምሰ | ጣፋጭ ታሪኮችና ወጎች

የልብ ነገር
ክፍል ሰባት
(ፉአድ ሙና)
***

አመመኝ አልልም
አልተነካም ጅስሜ፣
ጤነኛ አልምሰልሽ
ብታይ ስሄድ ቆሜ!

የሩሄን እህህታ
ጆሮ መቸ ሰምታ፣
ቧጥጬው ልሞት ነው
ልቤን ጠዋት ማታ!

***
አህመድ ሰሞኑን ቋሚ ፕሮጀክቱ አድርጎኛል። አላውቅም ምናልባት በሹራ ተመድቦብኝም ሊሆን ይችላል። ድንቄም ሹራ! ብሞት እንኳን የማያውቅ ጀመዓ! ከሁሉም የገረመኝ ግን ይህን ያህል ጊዜ ከመስጂድ ስርቅ ምን ሆኖ ይሆን ብሎ የጠየቀኝና ያስፈለገኝ ሰው አለመኖሩ ነው። አላህ ይስጣቸውና የተብሊግ ጀመዓዎች ብቻ ቤት የምሆንባቸውን ጊዜያት እየጠበቁ ሊዘይሩኝ ይመጣሉ። መጀመሪያ ሰሞን ሀያዕ እያደረግኩ አብሬያቸው ወደ መስጂድ እሄድ ነበር። ትንሽ ሲቆይ ግን አንኳኩተው «ወንዶች አሉ?» ሲሉ ዝም ማለት ጀመርን። ሰራተኛዋ ዝም ካልኩ መውጣት እንዳልፈለግኩ ስለምትረዳ፤ የለም ብላ ታሰናብታቸዋለች። ፌሪ በነበረችባቸው ጊዜያት ቀድማኝ «የሉም በያቸው!» ትላለች። በዕረፍት ቀናችን ትቻት ከቤት እንድወጣ አትፈልግም።

ባላወራውም ሁሌ በልቤ የታዘብኩት ግን ከትልቁ መስጂድ ሰዎች ውስጥ ከአህመድ በቀር የዘየረኝ አለመኖሩ ነው። አህመድም የግል ጓደኛዬ ስለሆነ እንጂ ባይሆን የሚዘይረኝ አይመስለኝም። ትልቁ መስጂድ ላይ በጣም ከሚንቀሳቀሱ ወጣቶች ግንባር ቀደም ነበርኩ። ከመስጂድ ስጠፋ ግን የፈለገኝ አልነበረም። እንደውም በተገላቢጦሹ የትንሹ መስጂድ ተብሊግ ጀመዓ የለም እየተባሉና በር እየተዘጋባቸው እንኳን እኔን ከመፈለግ አልቦዘኑም። ትልቁ መስጂድ ሰለፍይ ነን የሚሉ ጅሎች የሞሉት ነው። ጅሎች ያልኳቸው ስላልፈለጉኝ ነው። ምንም አይነት ሰዋዊ ግንኙነት የሌለው ማሽን የሚመስል ስብስብ ነው። ሰላት መስገድ እና ቂርዓት መቀመጥ እንጂ ከዚህ የዘለለ ሰዋዊ መስተጋብር የለውም። አሊሞቻቸውን እንኳን የሚያውቋቸው ሲሞቱ ነው። ሰላት እንደተሰገደ ሰው ትከሻ ላይ እየዘለሉ መሮጥ የሚወዱ ሰርከሰኞች የሞሉበት ነው። አሁን ወደ ትልቁ መስጂድ ብሄድ «የት ጠፍተህ ነበር?» ብሎ የሚያዋክበኝ ብዛቱ! ልሙት ልኑር ሳያጣሩ ስመለስ ማዋከብ ምን የሚሉት ነው? ከትልቁ መስጂድ ስልክ ከተደወለ ቃል የገባሁት ብር አለ ማለት ነው። ገንዘብ ሲፈልጉ ብቻ ይፈልጉኛል። አሁን የዛን መስጂድ አዛን መስማት ራሱ ያስጠላኛል። የፊርቃ ሰው አይደለሁም እንጂ ብሆን ኖሮ በእነሱ እልህ አዲስ ፊርቃ እመሰርት ነበር። አብዛኛውን ሰው ፊርቃ የሚያስቀይረው እልህ ይመስለኛል።

እሁድ ከሰዓት ነው። አህመዴ የአስር ሰላትን ትልቁ መስጂድ እንድንሰግድ ቃል አስገብቶኛል። ቃሌን ለመጠበቅ ሰዓቴን በተደጋጋሚ ተመለከትኩት።
«ምነው? ደረሰ እንዴ?» አለች ደረቴ ላይ እንደተጋደመች።
ኢክሩ ቤቴ ቤቷ ከሆነ ሰንብቷል።
«አይ አንድ ሰዓት ይቀረዋል ነገር መሰለኝ።»
«ሻወር እስክንወስድ ምናምን ጊዜ ስለምንፈጅ አሁን እንነሳ!» ከደረቴ ላይ ተነስታ ፀጉሯን ማስተካከል ጀመረች።
ስልኬ ጠራ። አህሜ መስሎኝ ነበር። ስመለከተው ፌሪ ናት።
«ማነው?» አለች ኢክሩ እየተጠጋችኝ!
«ፌሪ ናት .... እንደተለመደው እሺ!»
«አያሳስብም!»
ከኢክራም ጋር በጣም ከመላመዳችን የተነሳ ፌሪ ስትደውል ሚናችንን በአግባቡ እንወጣለን። ፌሪ አሳየኝ የምትለው ነገር ካለ ኢክሩ ኮተቷ ካሜራ ውስጥ እንዳይገባ በማድረግ ታግዘኛለች። እሷም ከካሜራው ጀርባ ሆና ትከተለኛለች።
ስልኩን አንስቼ ከፌሪ ጋር አወራን። ለመመለስ ሁለት ወራት ብቻ እንደቀሯት አበሰረችኝ። ብስራት ነው ግን? ምንም ደስታ አልሰማ አለኝ። እንደውም ጭንቀት ጭንቀት አለኝ። በራቀ በራቀ የሚል ስሜት ይወረኛል።
ስልኩን አናግሬ እንደጨረስኩ አንድ ላይ ወደ ሻወር ገባን። ምን ልትሰሩ የሚል የዋህ ካለ ልንታጠብ በሉልኝ። «ታጥበን» እንደጨረስን የምለብሰውን ልብስ ኢክሩ መምረጥ ጀመረች።
«ዛሬ ሼኪ ነው ‘ማስመስልህ!»
ጀለቢያዎቼን እያነሳች ትጥላለች። አንድ ወደ ጥቁረት የሚያደላ ጀለቢያ አነሳችና ወደኔ ይዛው መጣች። በቅርቡ ለኢድ የገዛሁት ነበር።
«ይኼ አብሮ ይሄዳል። ጁሙዓ ቢሆን ነጭ እናደርገው ነበር። እሁድ ስለሆነ ....  ስለምትንቀሳቀሱም ይሄ የበለጠ አብሮ ይሄዳል።»
«ጀለቢያ ይሻላል አልሽ?»
«አዎ ባክህ! እና ጥምጣም ደግሞ .... »
«ኧረ በአላህ በቃ እንዴ! መስጂድ ከሄድኩ ስንት ጊዜዬ ነው .... አይን ውስጥ አታስገቢኝ!»
«ማን ምን ያመጣል? ንፁህ ነው እንዴ የሚመስሉህ?»
«ይኼ ኮንፊደንስሽ እኮ ነው ደስ የሚለኝ!» ፈገግ አልኩላት።
የግቢያችን በር ሲከፈት ሰማንና፤ ተከታትለን ወደ መስታወቱ ሄድን። የአህመድ መኪና እየገባች ነው። ሳቅኩኝ።
«ይኼ ልጅ የምቀጣው መስሎት ከቤት ሊያግተኝ መጣ አይደል?»
«ጀለስህ ነው?»
«አዎ! ልበሺ ወደ ላይ ከመጣ ዘመዴ ናት እለዋለሁ።»
«እሺ አባያ አለኝ መኪናዬ ውስጥ! ሰራተኛዋ ይዛልኝ ትምጣ አንተ ታች አቆየው!»
ቀድሜ ወደታች ወረድኩ። ሰራተኛዋ አባያውን ወሰደችላት።

«አንተ! ይህን ያህል አታምነኝም?»
«እሱ እንኳን አላምንህም .... ግን በዚሁ ሰሚር አንሳኝ ብሎኝ እሱን አንስቼ መምጣቴ ነው።»
«እንዴ ሰሚሬ! እሱ ልጅ አለ በአላህ?»
«መኪና ውስጥ ተቀምጧል። ከገባ እንዳንቆይ ብዬ ተቀመጥ አልኩት።»
ኢክራም አባያዋን ለብሳ መጣች። አምሮባታል። የቤት እመቤት መስላለች።
«አሰላሙአለይኩም!» ፈገግ ብላ ተቀላቀለችን።
ለምን ወደ ታች እንደወረደች ግራ ተጋብቻለሁ። እንድትሰተር የፈለግኩት ወደ ላይ ካልወጣሁ ብሎ ካስቸገረኝ ብዬ ነበር።
«ወአለይኩሙሰላም!» አህሜ መለሰ። መጥታ ከአጠገቤ ተቀመጠች።
አህሜ በመገረም ይመለከተኛል።
በልቤ ምናባቷ ብላ እንደምትተዋወቅ እየሰጋሁ «ተዋወቁ ....» አልኩኝ።
«አህመድ እባላለሁ የባልሽ ጓደኛ ነኝ ....» ሳቀ። እኛም ሳቅን። መንገድ እየመራት እንደሆነ ገብቶኛል። ልጅት ግን የዋዛ አልነበረችም።
«ኢክራም እባላለሁ። ባሌ እንኳን አይደለም። ቤተሰብ ነን።»
ሌላ ምርመራ እንዳይጀምር ስለሰጋሁ «እንውጣ አይደል?» አልኩ እየተነሳሁ!
«አዎ አዎ! ሰሚሬም ይደብረዋል።»
ኢክራሜን ተሰናብተን ወደ መኪናው ሄድን።

ሰሚር ማለት የጀመዓችን ቀልደኛ እና ተጫዋች ነው። ከተጫዋችነቱ በተጨማሪ ደግሞ በሴት አጫዋችነቱ የ ISO የጥራት ማረጋገጫ የተሰጠው ወዳጃችን ነው። እሱ ካለ ስለሴት ማውራት ግዴታ ነው። ከግቢው ወጥተን ወደ መስጂድ መሄድ ጀመርን። አህመድ አላስቻለውም።
«ስማማ ፉአዴ!»
«እሺ!»
«ዝምድናችሁ የምንድነው ከልጅቷ ጋር?»
«ከኢክራም ጋር?»
«አዎ! ማለቴ ጋብቻ የሚከለክል ነው?»
«አይደለም!»
«ስትር ማለቷ እንዴት ደስ ይላል! ኧረ አትፍዘዝ!»
«ምን ላድርጋት?»
«አግባታ!»
«አይ አህሜ! ፈሪሀን የምትበቀልበት አጋጣሚ አገኘሀ!» ሳቅን።
«ባክህ አግባባት ስርዓት ትይዛለች ያቺም!»
«ቀልደኛ!»
«ካልሆነ ወደኔ ላከው .... አስተናግድልሀለሁ!» ሰሚሬ ተቀላቀለን።

መስጂድ ስንደርስ ጠያቂ እንደ ንብ መንጋ ሰፈረብኝ። የት ነበርክ? ከሀገር ወጥተህ ነው? ሰፈር ቀየርክ እንዴ? ምናምን! በልቤ «መች ፈለጋችሁኝ?» እያልኩ እገረማለሁ። የመጀመሪያ ጀመዓ አምልጦን ስለነበር ሁለተኛ ጀመዓ ቆምን። እኔን እንዳሰግድ ጋበዙኝ። እምቢ አልኩ።
«አንተ እያለህማ እኛ አንገባም!»
በግድ ገባሁ። ከደቂቃዎች በፊት ከኢክራም ጋር የነበርኩበት ሁኔታ እና አሁን የቆምኩበት ቦታ ተምታቱብኝ። ቆዳችን አይጮህም። እጆቻችን አያወሩም። ሀፍረታችን አይናገርም። ልብስ ብዙ ነገር ይሸፍናል! እጅግ ብዙ! ለዚህ ፀጋው ከማመስገን ውጪ ምን እላለሁ? ምንም!