2022-07-16 21:56:56
ቅዳሜ ሐምሌ 9/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች
1፤ ፌደሬሽን ምክር ቤት ለውስን ዓላማ የሚደረግ የበጀት ድጎማን እና የፌደራል መሠረተ ልማትን ፍትሃዊ ሥርጭት ለመከታተል የሚያስችለውን ሥርዓት ለማስፈጸም የተረቀቀ ደንብ ማጽደቁን አስታውቋል። ደንቡ በክልሎች የመሠረተ ልማት ግንባታ በሚያካሂዱ የፌደራል ተቋማት እና ፌደራል መንግሥት ለክልሎች በሚመድበው ውስን ዓላማ ያላቸው ድጎማዎች ላይ ተግባራዊ የሚሆን ነው።
2፤ የመንግሥት የጸጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በደቡብ ክልል በክልልነት በመደራጀት ጥያቄ ስም ግጭት እና አመጽ የሚቀሰቅሱ አካላትን እንደማይታገስ ትናንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የደቡብ ክልል መንግሥት ዞኖቹን እንደገና ለማዋቀር ጥረት ላይ መሆኑን የገለጠው ግብረ ኃይሉ፣ የጌዲኦ ዞን ጥያቄን በኃይል ለማስፈጸም በኅቡዕ ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ አካላት እንዳሉ ደርሼበታለሁ ብሏል። ግብረ ኃይሉ ጨምሮም፣ እነዚሁ አካላት በማኅበራዊ ትስስር ዘዴዎች ሐሰተኛ መረጃዎችን እያሰራጩ እና የቤት ለቤት ቅስቀሳ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጧል።
3፤ ታጣቂዎች በደቡብ ክልል ቡርጂ ልዩ ወረዳ ባደረሱት ጥቃት አራት ሰዎች ተገድለው አምስቱ እንደቆሰሉ ቪኦኤ የአካባቢውን ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል። የታጣቂ ቡድኑ ታጣቂዎች በአጎራባቹ አማሮ ልዩ ወረዳ ላይ ጭምር በፈጸሙት ተመሳሳይ ጥቃት፣ አንድ አርሶ አደር ገድለው በርካታ እንስሳትን ዘርፈዋል ተብሏል። ታጣቂ ቡድኑ ከቡርጂ ወረዳ አጎራባች ከኦሮሚያው ምዕራብ ጉጂ ዞን የሚነሳ እንደሆነ ተገልጧል።
4፤ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ማቋቋሚያ ቻርተር ያሻሻለ ረቂቅ እንዳዘጋጀ ገለፀ። የተሻሻለው ረቂቅ ቻርተር፣ በሕግ ማውጣት፣ ማስፈጸም እና መተርጎም ሂደት ቅሬታ ይቀርብባቸው በነበሩ አንቀጾች እና በከተማዋ የገቢ ክፍፍል ጉዳይ ላይ የማሻሻያ ሃሳቦችን ይዟል። ረቂቅ ቻርተሩ የከተማዋ ፖሊስ ተጠሪነት ለከተማዋ አስተዳደር እንዲሆንም ሃሳብ አቅርቧል። ረቂቅ ቻርተሩ ሥራ ላይ የሚውለው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካጸደቀው ነው።
5. አሀዱ ባንክ 23ኛው የግል ባንክ ሆኖ ዛሬ በይፋ ተመርቆ ስራ ይጀምራል::
አሃዱ ባንክ በ564 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል 10 ሺህ ባለ ድርሻዎችን ይዞ ዛሬ ወደ ባንክ ገበያ መቀላቀሉን አስታውቋል። ብሄራዊ ባንክ አዲስ ለሚቋቋሙ ባንኮች ያስቀመጠው ዝቅተኛው የተከፈለ ካፒታል መጠን 500 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ባንኩ ግን በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት በአዲሱ የብሄራዊ ባንክ መመሪያ መሠረት ካፒታሉን ወደ 5 ቢሊዮን ብር እንደሚያሳድግ ገልጧል። ባንኩ እስከ መስከረም ቅርንጫፎቹን 50 እንደሚያደርስ እና ወደፊት 70 በመቶ ቅርንጫፎቹ በገጠሮች ከፍቶ ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግሯል።
6፤ በኬንያ ጉብኝት ላይ ያሉት የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር የንግድ እና ዲፕሎማሲያዊ ስምምነቶችን መፈራረማቸውን የኬንያ ጋዜጦች ዘግበዋል። በስምምነቱ መሠረት ኬንያ ታግዶባት የቆየውን የጫት ምርቷን ወደ ሱማሊያ መላክ የምትጀምር ሲሆን፣ ሱማሊያ ደሞ የአሳ ምርቶችን ወደ ኬንያ ትልካለች። የኬንያ አየር መንገድም አቋርጦት የነበረውን የሞቃዲሾ በረራውን እንደገና ይጀምራል።
7፤ በሱማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም ተልዕኮ በሱማሊያ 160 ናይጀሪያዊያን ፖሊሶችን ማሰማራቱን አስታውቋል። ፖሊሶቹ ቀደም ሲል ተልዕኳቸውን ያጠናቀቁ የናይጀሪያ ፖሊሶችን የሚተኩ ናቸው። በተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት፣ የሱማሊያ የሰላም ተልዕኮ ለአገሪቱ ፖሊስ ሠራዊት ድጋፍ የሚሰጡ አንድ ሺህ አርባ ፖሊሶች ይኖሩታል። በሱማሊያ ፖሊስ ኃይል ያሠማሩት፣ ኬንያ፣ ናይጀሪያ፣ ጋና፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ሴራሊዮን ናቸው።
@Ethiopianewsagency (ኢዜአ)
186 viewsedited 18:56