Get Mystery Box with random crypto!

ማክሰኞ ሐምሌ 19/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የሱማሌ ክልል ልዩ ኃይል በድጋሚ የኢትዮ-ሱ | ኢ.ዜ.አ

ማክሰኞ ሐምሌ 19/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ የሱማሌ ክልል ልዩ ኃይል በድጋሚ የኢትዮ-ሱማሊያን ድንበር አቋርጠው ከገቡ የአልሸባብ ተዋጊዎች ጋር ትናንት መፋለማቸውን የክልሉ ኮምንኬሽን ቢሮ አስታውቋል። ታጣቂዎቹ ከሱማሊያዋ ሂራን ግዛት በመነሳት ወደ ሸበሌ ዞን ፌርፌር ወረዳ እንደገቡ የጠቀሰው ቢሮው፣ ልዩ ስሟ "ኤል ቀዱን" በተባለች ቦታ ላይ ተመተዋል ብሏል። የክልሉ መንግሥት ከአልሸባብ ጋር በድጋሚ ውጊያ እንደተደረገ የገለጠው፣ መከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው መዝመቱን ከገለጸ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነው።

2፤ የፌደራል ገቢዎች ሚንስቴር በትግራይ ክልል የተመዘገቡና ባሁኑ ወቅት ከክልሉ ውጭ ከሚገኙ የክልልና የፌደራል ግብር ከፋዮች ግብር ሊሰበስብ መሆኑን ገለፀ። ሚንስቴሩ ለክልሉ ገቢ መሆን ያለበትን ግብር በአደራ ባንክ ለማስቀመጥ አቅዷል። በጦርነቱን ሳቢያ ግብር ከፋዮች ብድር ለማግኘትና በጨረታ ለመወዳደር ተቸግረው ቆይተዋል። ግብር ከፋዮቹ ትግራይ ውስጥ ያለባቸው ዕዳ ስለማይታወቅ፣ ሚንስቴሩ ከፋዮቹ የሚያሳውቁትን ግብር ብቻ ይሰበስባል።

3፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ተመድ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲመረምር ላቋቋመው ገለልተኛ መርማሪ ኮሚሽን የሾማቸውን ኮሚሽነሮች ትናንት በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው እንዳነጋገሩ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል። ለስድስት ቀናት ጉብኝት ትናንት ኢትዮጵያ የገቡት መርማሪ ኮሚሽነሮች፣ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ኬንያዊቷ ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ፣ አሜሪካዊው ስቲቨን ራትነር እና ሽሪላንካዊቷ ኩማራስዋሚ ናቸው።

4፤ የሱማሊያ ፓርላማ ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዛ ባሬ አዲሱን ካቢኔያቸውን እንዲያቋቁሙ 10 ተጨማሪ ቀናት እንደሰጣቸው የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ተጨማሪ ቀናት የተሰጣቸው፣ ቃለ መሃላ በፈጸሙ በ30 ቀናት ውስጥ ካቢኔ ማቋቋም ባለመቻላቸው ነው። በሱማሊያ ታሪክ አንድ ጠቅላይ ሚንስትር ባንድ ወር ውስጥ ካቢኔ ባለማቋቋም የአሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል። ባሁኗ ሱማሊያ የተለያዩ ጎሳዎች የካቢኔ ሥልጣን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረቶችን እንደሚያደርጉ ይታወቃል።

5፤ ዩክሬን በተያዘው ሳምንት ወደቧ ላይ የተሰማቸውን የጥራጥሬ ምርቷን ለውጭ ገበያ እንደምታቀርብ መግለጧን ዓለማቀፍ የዜና ወኪሎች ዘግበዋል። ከኦዴሳ እና ሌሎች ወደቦች ከ20 ሚሊዮን ቶን በላይ የምግብ እህል እንደተከማቸ ይገመታል። የዓለም ምግብ ድርጅት ግን፣ የዩክሬን እህል ምርት ለገበያ እንዲቀርብ ሩሲያና ዩክሬን በቅርቡ የደረሱበት ስምምነት ብቻውን በዓለም ላይ የተከሰተውን የምግብ ዋጋ ውድነት አይቀርፍም ብሏል።

6፤ የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ዛሬ በኡጋንዳ በሚያደርጉት ጉብኝት ከፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቪኒ ጋር እንደሚወያዩ ዓለማቀፍ የዜና ወኪሎች ዘግበዋል። የኡጋንዳ መንግሥታዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሩሲያውን "አርቲ" ቴሌቪዥን ዝግጅቶች በቀን ሁለት ጊዜ ለማሰራጨት ቀደም ሲል ተስማምቷል። ላቭሮቭ በግብጽ፣ ኮንጎ፣ ኡጋንዳና ኢትዮጵያ ጉብኝት የሚያደርጉት፣ በዩክሬኑ ጦርነት ሳቢያ የምዕራባዊያን ማዕቀብ ሰለባ ለሆነችው አገራቸው የአፍሪካ አገራትን ድጋፍ ለማግኘት እንደሆነ ተገምቷል።

@Ethiopianewsagency (ኢዜአ)