Get Mystery Box with random crypto!

ሰኞ ሐምሌ 18/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች 1፤ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በሰሜን ኢ | ኢ.ዜ.አ

ሰኞ ሐምሌ 18/2014 ዓ.ም ዐበይት ዜናዎች

1፤ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተፈጸሙ ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲመረምር ባለፈው ታኅሳስ ያቋቋመው መርማሪ ኮሚሲዮን ኮሚሽነሮች ከዛሬ እስከ ቅዳሜ በኢትዮጵያ ጉብኝት ላይ መሆናቸውን ምክር ቤቱ አስታውቋል። ሦስቱ ኮሚሽነሮች በመጭው ቅዳሜ የጉብኝታቸውን ውጤት አስመልክተው ከተለያዩ አካላት ጋር ይወያያሉ። ሦስት ኮሚሽነሮች ያሉት ኮሚሲዮን ምርመራውን በቅርበት እንዲያከናውን ካምፓላ ላይ ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞለታል።

2፤ መከላከያ ሠራዊት የሱማሊያውን አልሸባብ ለመፋለም ወደ ኢትዮ-ሱማሊያ ድንበር መሠማራቱን የሱማሌ ክልል ኮምንኬሽን ቢሮ አስታውቋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ኡመር ባካባቢው ከክልሉ ልዩ ኃይል ጋር የተቀላቀሉትን የሠራዊቱ አባላት ጎብኝተዋል። ባለፉት ቀናት የክልሉ ልዩ ኃይል በአፍዴር ዞን በኩል ወደ ሱማሌ ክልል በገቡት የአልሸባብ ተዋጊዎች ላይ ልዩ ስሙ ሁልሁል በተባለ ቦታ ላይ፣ በርካታ የቡድኑን ታጣቂዎች መግደላቸውና ጦር መሳሪያዎችን መማረካቸውን የክልሉ መንግሥት መግለጡ ይታወሳል።

3፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በመጭው ዓመት 30 ሚሊዮን ብር በጀት ያስፈልገኛል ሲል ዛሬ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ገለጠ። ምክር ቤቱ በጀቱን የፈለገው፣ የአባል ፖለቲካ ፓርቲዎችን አቅም ለመገንባት እና በአገራዊ ምክክሩና በአካባቢያዊ ምርጫዎች ዓይነተኛ ተሳትፎ ለማድረግ እንዲችል መሆኑን ተናግሯል። ምክር ቤቱ አብዛኛውን ገንዘብ ለማግኘት ያቀደው ከዓለማቀፍ ለጋሾች ነው።

4፤ ሳፋሪኮም ኩባንያ በኢትዮጵያ ቴሌኮም ዘርፍ ለመሠማራት ከአሜሪካው ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ላገኘው አገልግሎት 4 ሚሊዮን ዶላር እንደከፈለ ቢዝነስ ደይሊ ዘግቧል። ኮርፖሬሽኑ ምን አገልግሎት እንደሰጠ ኩባንያው ባይገልጽም፣ በኢትዮጵያው የቴሌኮም ጨረታ የምክር አገልግሎት መስጠት ወይም ዓለማቀፍ ብድሮችን ማስገኘት ሊሆን እንደሚችል ዘገባው ጠቁሟል። የናይሮቢው ስታንዳርድ ቻርተርድ ባንክ ብቻ ለኩባንያው 400 ሚሊዮን ዶላር አበድሯል። ሳፋሪኮም በነሐሴ በድሬዳዋ ሥራውን ይጀምራል።

5፤ የሱማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ዛሬ ከግብጹ አቻቸው አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ቤተ መንግሥታቸው አስታውቋል። ሁለቱ መሪዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በሁለትዮሽ እና የቀይ ባሕር አካባቢ ደኅንነትን ጨምሮ በቀጠናዊ ጸጥታና ልማት ዙሪያ መወያየታቸውን ተናግረዋል። ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ፣ ከግብጽ ቀደም ብሎ በኤርትራ፣ ጅቡቲና ኬንያ ኦፊሴላዊ ጉብኝት አድርገዋል።

6፤ የሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የግብጽ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ዛሬ ኮንጎ ብራዛቪል እንደገቡ ዓለማቀፍ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። አገራቸው ከዩክሬን ጋር በገባችበት ጦርነት ሳቢያ ምዕራባዊያን ማዕቀብ ከጣሉባት ወዲህ፣ ላቭሮቭ በአፍሪካ ተከታታይ ጉብኝቶችን ሲያደርጉ የመጀመሪያቸው ነው። ላቭሮቭ ከኮንጎ ብራዛቪል ቀጥሎ ኡጋንዳንና ኢትዮጵያን የሚጎበኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከአፍሪካ ኅብረት ባለሥልጣናት ጋር ጭምር እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል። ከወር በፊት የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ሩሲያን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

7፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 52 ብር ከ1166 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 53 ብር ከ1589 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 59 ብር ከ4718 ሳንቲም፣ መሸጫው 60 ብር ከ6612 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ52 ብር ከ9661 ሳንቲም ሲገዛ እና በ54 ብር ከ0254 ሳንቲም ሲሸጥ ውሏል።

@Ethiopianewsagency (ኢዜአ)