Get Mystery Box with random crypto!

ሦስት የሕንጻ ቀለማት ለሙከራ ተመርጠዋል። ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የአ | Ethiopian Architecture Construction and Urbanism

ሦስት የሕንጻ ቀለማት ለሙከራ ተመርጠዋል።


ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ)

የአዲስ አበባ ከተማ የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ሦስት አይነት የሕንጻ መቀቢያ ቀለማት ለሙከራ መመረጣቸውን ገለጸ፡፡

የመዲናዋን የውበት ደረጃ የተጠበቀ ይሆን ዘንድ የሕንጻ ቀለም መምርጥ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ ሦስት አይነት ቀለማት ለሙከራ መመረጣቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የሕንጻ መጠቀሚያ ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሄኖክ ለጋሳይ ተናግረዋል፡፡

የተመረጡት ቀለማት ግሬይ (ግራጫ)፤ ነጭ እና አልሙኒየም መሆናቸውን ተቋሙ በዛሬው ዕለት በአዜማን ሆቴል በሰጠው መግለጫ ላይ ሄኖክ አብራርተዋል፡፡

ጥናት ላይ መሰረት ተደርጎ ነው የቀለማት ምርጫ የተደረገው ያሉት ሄኖክ፤ ለአብነትም 65 በመቶ የሚሆነው ሕዝቦች የግራጫ ቀለም ተጠቃሚዎች መሆናቸው በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

በከተማዋ የሚሰተዋለው የሕንጻ ቀለም ቅብ ዝብርቅርቅ በመሆኑ የከተማዋን ውበት ሳያደበዝዝ አልቀረም የተባለ ሲሆን፤ ሥርዓታዊ በሆነ መልኩ ሦስቱን ቀለማት በመጠቀም የከተማዋን ውበት ለማዘመን ይቻላል ነው የተባለው፡፡

ሦስቱን ቀለማት በማስማማት በተለያዩ ቀይ፤ ቢጫና ሌሎች ደማቅ ቀለማት የተቀቡትን ሕንጻዎች ማስዋብ ሙከራ እንደሚደረግና የማሕበረሰቡን አስተያየት መሰረት በማድረግ እንየኹኔታው ማስተካከያ እንደሚሰጥም ተብራርቷል፡፡

ከተማችን የአለማቀፍ ድፕሎማቶች መገኛ ናት ያሉት ሄኖክ፤ ጅማሮው ሕንጻዎች በየፈርጃቸው ውጥነት ባለው ቀለም ተቀብተው ደረጃቸው በመጠበቅ ለእይታ ሳቢ እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ስለመገኘቱም አንስተዋል፡፡

ቀለማቱ ቋሚነት የሚኖራቸው በሙከራ ከታዩ በኋላ በሚገኘው አስተያየት ነው የተባለ ሲሆን፤ አልሙኒየም ቀለም በቸርችል ጎዳና ስለመሞከሩም ለአብነት ተነስቷል፡፡

ተቋሙ በነበረው መግለጫ የከተማዋን ውበት ያደበዘዙ ተለጣፊ፤ ተንጠልጣይ እና ማስታዎቂያዎችን በተመለከተም ማሻሻያ እንደሚደረግና እየተደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

በኢዮብ ትኩዬ

ምንጭ አዲስ ማለዳ
@ethiopianarchitectureandurbanism