Get Mystery Box with random crypto!

ከትንሣኤ በኋላ ያሉ ዕለታት ሰኞ ሰኑይ ማእዶት ይባላል እንደ ቤተክርስቲያን ይትባሕል ከትንሣ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ከትንሣኤ በኋላ ያሉ ዕለታት
ሰኞ
ሰኑይ ማእዶት
ይባላል
እንደ ቤተክርስቲያን ይትባሕል ከትንሣኤ እስከ ዳግማዊ ትንሣኤ ያለውን ሳምንት እንደ አንድ እሁድ እናከብራለን። ለዚህም ነው ዕለታቱን እንደ ሰንበት እናከብራቸው ዘንድ በፍትሐ ነገሥት ላይ አባቶቻችን ትእዛዝ የቀረጹልን።
ማእዶት ማለት መሻገር ማለት ነው። አደወ ማለት ተሻገረ ማለት ሲሆን ማእዶት መሸጋገሪያ ማለት ሊሆን ነው።
ማእዶት የትንሣኤ እሑድ ማግስት ጌታ ክርስቶስ በትንሣኤው ምዕመናንን ከሞት ወደ ሕይወት ያሻገረበት ቀን የትንሣኤው ማሳሰቢያ ነው። (ከሣቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ገጽ ፻፶)
መሻገር በዕብራይስጥ ፓሳሕ ከሚባለው ቃል ይመሳሰላል ትርጉሙም ፋሲካ መሻገር ማለፍ የሚል ትርጉም ይሰጣል። ሁላችን እንደምናውቀው እስራኤላውያን ከሚያክብሯቸው አበይት በዓላት አንዱም ፋሲካ ነው። ምክንያታቸው ደግሞ እግዚአብሔር ከሞተ በኩር ያሳለፋቸውን ዕለት ያስቡበታል።
ቤተክርስቲያናችንም ይህንን በዓለ ትንሣኤን የፋሲካ በዓል የማክበሯ ምሥጢር ወይም የትንሣኤው ምሥጢር ነፍሳት በአምላካችን ትንሣኤ ከሞት ወደ ሕይወት ፣ ከአሳር ወደ ክብር ፣ ከሲዖል ወደ ገነት መሻገራቸውን በማሰብ አማናዊው ፋሲካ ወይም አሸጋጋሪው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ብላ ታምናለች። እናምናለን።
ቅዱስ ጳውሎስ በብሉይ ኪዳን በታረደው የፋሲካ በግ (ዘዳ፲፮:፮) ምትክ አማናዊው ክርስቶስ እንደታረደልን እና ሞት ላያገኘን በሕይወት ለሕይወት እንዳሸጋገረን ሲገልጥ እንዲህ ብሏል:-"" እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ
አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና፤" (፩ ቆሮ ፭:፯)
ቅዱስ ጳውሎስ ስለ እርሾም ሆነ ስለ አዲሱ ሊጥ በምሳሌ የሚነግረን እስራኤላውያን የእግዚአብሔርን ፋሲካ ሲያከብሩ ያደርጉት የነበረ ስርዓትን ነው።
ይኸውም ፋሲካን ያከበሩት ገና ከነጻነት በፊት ነው። ምክንያቱ ደግሞ ከላይ እንዳየነው ከሞተ በኩር መቅሰፍት ለመዳን እና ከእግዚአብሔር ፍርድ ለመዳን ነበር።
በአዲስ ኪዳንም ያለን ክርስቲያኖች በተለይ ይህንን ዕለት ወይም ማእዶትን ስናስብ አምላካችን ከሞት ወደ ሕይወት እንዳሻገረን ፣ ከአሳር ወደ ክብር እንዳሳለፈን ፣ ከድካም ወደ ኃይል እንዳሻገረን ፣ ሁላችን ወደ መንግሥተ
ሰማያት ፋሲካችን በሆነው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተሸጋገርን በማመን ሊሆን ይገባል።
የፋሲካው ጌታ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞት ላይ እንድንዘባበትበት ሞትን ፣ ፍርሃትን ፣ ጭንቀትን ፣ ተስፋ መቁረጥን ፣ ሐዘንን ፣ ለቅሶን ፣ ትካዜን ፣ ድካምን ፣ ሥጋትን እና መቃብርን ሁሉ አጥፍቶ አሻግሮናል። ክብር ማዕዶታችን
ለሆነ ለእርሱ ይሁን። አሜን ክብር ይግባውና አምላካችን የሰው ልጅ ሞትን እንዲሻገር ሁለት ነገሮች(እምነት እና ምግባር ) እንደሚያስፈልጉት በመዋለ ስብከቱ እንዲህ ሲል አስተምሮናል:-
"እውነት እውነት እላችኋለሁ ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።
እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል እርሱም አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።" (ዮሐ፭:፳፬-፳፭)
ሊቁ ቅዱስ ያሬድም ዕለቷ ፋሲካ እንደሆነችና እንደሰትባት ዘንድ የተገባች እንደሆነች እንዲህ ሲል በመዝሙሩ አዚሞታል:- " ፋሲካ ዛቲ ዕለት ቅድስት ይእቲ (ይህቺ የፋሲካ ዕለት ልዩ ናት) ፣ ዛቲ ዕለት ንትፈሳሕ በቲ (በዚህ ዕለት ሐሴት እናድርግባት)..."

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox