Get Mystery Box with random crypto!

ጭፍሮቹም በዚሁ ዕለት ሌሊት የክብር ባለቤት የሆነውን ጌታችንን ይዘው ወደፊት፣ ወደኋላ እየጐተቱ፣ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ጭፍሮቹም በዚሁ ዕለት ሌሊት የክብር ባለቤት የሆነውን ጌታችንን ይዘው ወደፊት፣ ወደኋላ እየጐተቱ፣ እያዳፉ ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ወስደውታል።

መዝሙረ ዳዊት ምንባባት
በአንድ ሰዓት፡- "አፉ ከቅቤ ይልቅ ለዘበ ፤ በልቡ ግን ሰልፍ ነበረ ፤ ቃሎቹም ከዘይት ይልቅ ለሰለሱ ፤ እነርሱ ግን እንደ ተመዘዘ ሰይፍ ናቸው" (መዝ፶፬(፶፭)፡፳፩)
በሦስት ሰዓት፡- "የጻድቅን ነፍስ ያደቡባታል፤ በንጹህ ደምም ይፈርዳሉ፡፡"(መዝ፺፫(፺፬):፳፩)
በስድስት ሠዓት፡- "የብዙ ሰዎችን ስድብ ሰምቻለሁና በዙሪያው ፍርሃት ነበረ በላዬ በአንድነት በተሰባሰቡ ጊዜ ፤ ነፍሴን ለመንጠቅ ተሰባሰቡ፡፡"(መዝ፴ (፴፩):፲፫
በዘጠኝ ሰዓት፡- "እግዚአብሔር እረኛዬ ነው ፤ የሚያሳጣኝም የለም ፤ በለመለመ መስክ ያሳድረኛል፡፡" መዝ፳፪(፳፫):፩-፪
ኅጽበተ እግር ሲጀመር ደግሞ "በሂሶጵ እርጨኝ እነጻማለው እጠበኝ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለው፡፡" (መዝ፶:(፶፩):፯)
በመጽሐፈ ግብረ ሕማማት፡- "ከዚህ በኋላ የእግር እጥበት ሥርዓት ነው ፤
ዲያቆን ሁለት ኩስኩስቶች ያቅርብ በውስጣቸውም ውኃ ይምላባቸው አንዱ
ለእጅ መታጠቢያ እንዲሆን ካህኑም እስከ መጨረሻው ጸሎተ አኮቴት ይበል ፤
ጸሎተ ዕጣኑንም ደግሞ ዕጣንን ያሳርግ ፤ ስለ ሰላም ስለ ሊቀ ጳጳሳት ስለ ማኅበር ይጸልይ፡፡ ሕዝቡም ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁንዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን ይበሉ፡፡ አነ ዘበሰማያትም ይበልሉ ፤ ኀምሳኛውንም የዳዊትን መዝሙር ይበሉ፡፡" (ግብረ ሕማማትገጽ፭፻፵፪)
"ከዚህ በኋላ ሕዝቡ ይነሱ አርባ አንድ ጊዜ ኪራላይሶን ይበሉ ካህኑም መስቀል ይዞ ውኃውን ሦስት ጊዜ አሐዱ አብ ቅዱስ (ልዩ ክቡር ንጹሕ ጽኑዕ ነው) ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ (ልዩ ክቡር ንጹሕ ጽኑዕ ነው) ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ (ልዩ ክቡር ንጹሕ ጽኑዕ ነው) እያለ ሦስት ጊዜ ውኃውን ይባርክ፡፡" (ግብረ ሕማማት ገጽ ፭፻፶፱)
"ከዚህ በኋላ ካህኑ እንደ ሥርዓቱ ኅጽበተ እግርን ያድርግ (ይፈጽም) ከዚህ በኋላም ጥቁር ልብስ ለብሰው ሥርዐተ ቅዳሴውን ይጀምሩ የቃጭል ድምጽንም አያሰሙ፡፡" (ግብረ ሕማማት ገጽ፭፻፷፩)
በአሥራ አንድ ሰዓት፡- "በፊቴ ገበታን አዘጋጀህልኝ በጠላቶቼ ፊት ለፊት ራሴን በዘይት ቀባህ ጽዋዬም የተረፈ ነው" (መዝ፳፪(፳፫):፭-፮)
የአይሁድ ካህናት ያለበደል እና ያለጥፋት ንጹውን ክርስቶስን ለመስቀል ሞት እንዲደርስ በጭካኔ በዕለተ ሐሙስ ከሌሊቱ 3፡00 ጀምሮ ብዙ መከራ አደረሱበት ፤ እጅጉን ተሰቃየ ፤ እያዳፉ አንዳች ሳይናገር አሰቃዩት ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ በትንቢት መነጽር የተመለከተውን የጌታችንን ስቃይ እንዲህ ሲል ያመጣዋል፡-
"ተጨነቀ ተሠቃየም አፉንም አልከፈተም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በማስጨነቅና በፍርድ ተወሰደ ስለ ሕዝቤ ኃጢአት ተመትቶ ከሕያዋን ምድር እንደተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ?ከክፉዎቹም ጋር መቃብሩን አደረጉ..."(ኢሳ፶፫:፩-፰)
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox