Get Mystery Box with random crypto!

የሰሙነ ሕማማት አምስተኛ ቀን ሐሙስ ከስቅለትና ከትንሣኤ በፊት ያው ሐሙስ በቤተክርስቲያን ልዩ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

የሰሙነ ሕማማት አምስተኛ ቀን
ሐሙስ

ከስቅለትና ከትንሣኤ በፊት ያው ሐሙስ በቤተክርስቲያን ልዩ ልዩ ስያሜዎች
አሉት፡፡
ሀ. ጸሎተ ሐሙስ ይባላል።
የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ይለምን ይማልድ የነበረን ሥጋን የተዋሐደ ፍጹም አምላክ፤ ፍጹም ሰው መሆኑን ለማጠየቅ ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ነው፤ (ማቴ 26፤36-46፣ ዮሐ.17)
ለ. ሕጽበተ ሐሙስ ይባላል ።
ሕጽበተ እግር፦ ይህ ስያሜ የተሰጠው ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት ነው፤ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳትና የደብር አስተዳዳሪዎች በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብሕን ኃጢአት እጠብ ሲሉ ከአገልጋዮቹ ጀምረው በቤተክርስቲያን የተገኙትን ምእመናን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ሲያጥቡ ያረፍዳሉ፡፡
ሐ. የምሥጢር ቀን ይባላል ።
ከሰባቱ ምሥጢራት አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷልና፤ ይኸውም ‹‹ይህ ስለእናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ ብሉ›› ጽዋውንም አንሥቶ አመሰገነ ‹‹ይህ ስለእናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ›› በማት እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ የምንሆንበትን መንገድ ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ቅዳሴ ይቀደሳል፤ የሚቀደሰውም በለሆሳስ ሲሆን እንደ ቃጭል ሆኖ የሚያገለግለውም ጸናጽል ነው፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ ሲመጡ ድምጻቸውን ዝግ አድርገው፣ በለሆሳስ እየተነጋገሩ መምጣታቸውን ለማሰብ ነው፤ በቅዳሴውም ጸሎተ ተአምኖ፣ ኑዛዜ አይደረግም፤ ሥርዓተ ቁርባን ግን ይፈጸምበታል፤ ይህም ጌታችን የሰጠውን ዘለዓለማዊ ቃል-ኪዳን ለማሰብ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ተዘጋጅቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ይኖርበታል፡፡
መ. የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡
ጸሎተ ሐሙስ ( የፋሲካ እራት) ፦ ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጐ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹ይህ ጽዋዕ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱም ጠጡ››በማለቱ ይታወቃል፡፡ (ሉቃ.22፤20) ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊ ቃል-ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት መሆኑን በማሰብ የቃል-ኪዳኑ ፍጻሜዎች፣ ጠባቂዎች መሆን እንደሚገባን እንማራለን፡፡
ሠ. የነጻነት ሐሙስ ይባላል።
ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባርያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ራሱ ጌታችን ስለሰው ልጅ ነፃነት ሲናገር ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፡፡›› በማለቱ(ዮሐ.15፤15) ከባርነት የወጣንበት ቀን መሆኑን መጽሐፍ በግልጥ ያስረዳናል፡፡
ስለዚህ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከኃጢአት ባርነት ተላቅቆ፤ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርበታል፡፡
እርሱ ጠላቶቹ ስንሆን ወዳጆቹ አድርጐናልና፡፡
ረ. አረንጓዴ ሐሙስ አምላካችን የጸለየበትን የአትክልት ቦታ ወይም ጌቴሴማኒ ለማሰብ ይህ ስያሜ ተሰጥቶታል።

ጌታ እንዴት ምን እና ለምን ጸለየ?
እንዴት ጸለየ?

አምላካችን የምሥጢር ሐዋርያቱን (ዮሐንስ ፣ ያዕቆብ እና ጴጥሮስ ) አምስት ትሕዛዝን (ተቀመጡ ፣ ትጉ ፣ ጸልዩ ፣ ተኙ ፣ ዕረፉ ) በማዘዝ ግንባሩን ምድር አስነክቶ ሰግዶ ጸለየ።(ማቴ፳፮:፴፮-፵፭)
ምን ጸለየ?
ሦስት ጊዜ ደጋግሞ የጸለየው ጸሎት አንድ ዓይነት ነው ይኸውም:- "አባቴ ቢቻልስ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ ፣ ነገር ግን አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ።"(ማቴ፳፮:፴፮-፵፭)
ለምን ጸለየ?
፩. ምሣሌ ይሆነን ዘንድ ነው።
፪. ፈቃዱን ማስቀደም እንዳለብን እናውቅ ዘንድ ነው።
፫. ወደፈተና እንዳንገባ መጸለይ እንደሚገባ እናውቅ ዘንድ ነው።
የጸሎቱ ትርጓሜ ምንድን ነው?
፩. ዓለም እንድትድን እና ክብርን እንድታገኝ ለሞት ተላልፎ እንደሚሰጥ ገልጿል።
"ያለ እኔ ሞት የዓለሙ ደኅንነት ያለ እኔ ሐሳር የዓለሙ ክብር አይቻልም እንጂ የሚቻልስ ከሆነ ይህ ጽዋዓ ሞት ይለፍልኝ። ነገር ግን ያንተ ፈቃድ ይደረግ እላለሁ እንጂ የኔ ፈቃድ ይደረግ አልልም።" (ወንጌል አንድምታ ገጽ፪፻፸፱)
፪. ሞት እንዲቀርልን እንደ ሞተ ገልጿል። "በኔ ሞት የዓለም ደኅንነት በኔ ኃሣር የዓለም ክብር የሚቻልስ ከሆነ እኔ ከሞትሁላቸው ከኔ ሞት የተነሳሣ ይህ ጽዋዕ ሞት ይቅርላቸው።(ወንጌል አንድምታ ገጽ፪፻፸፱)
፫. አብነት ይሆነን ዘንድ ሞትን እንደሚቀምስ ገልጿል። " ከኔ ለምዕመናን ይለፍላቸው ። እኔን አብነት አድርገው ይሙቱ ። ነገር ግን የኔ ፈቃድ ካንተ ፈቃድ ልዩ ሁኖ የኔ ፈቃድ ይሁን አልልም። የኔ ፈቃድ ካንተ ፈቃድ ጋራ አንድ ነውና ያንተ ፈቃድ ይሁን እላለሁ እንጂ። " (ወንጌል አንድምታ ገጽ፪፻፸፱)

በዚህ ዕለት በወንጌላት የተመዘገቡ ድርጊቶችን ቀጥለን እንመልከት፡
ሀ. የፋሲካ ዝግጅት የተደረገበት ዕለት ነው ።
ዝግጅቱ በሦስቱ ወንጌላት ላይ ተመዝግቧል፡፡ (ማቴ.26፤17-19፣ ማር 14፤1-16፣ ሉቃ.22፤6-13) ፋሲካ ማለት ማለፍ ማለት ነው፤ ይኸውም እሥራኤላውያን በግብጽ ምድር ሳሉ መልአኩን ልኮ እያንዳንዱ እሥራኤላዊ የበግ ጠቦት እንዲያርድና ደሙን በበሩ ወይንም በመቃኑ እንዲቀባ ለሙሴ ነገረው፤ ሙሴም ለሕዝቡ ነገረ፤ ሁሉም እንደታዘዙት ፈጸሙ፤ መቅሰፍተ ከእግዚአብሔር ታዞ መልአኩ የደም ምልክት የሌለበትን የየግብጻውያን ቤት በሞተ በኵር
ሲመታ፤ የበጉ ደም ምልክት የእሥራኤላውያንን ቤት ምልክቱን እያየ ማለፉን ለማመልከት ነው፡፡ (ዘዳ.12፤1-13) በዚህ መነሻነት በየዓመቱ እሥራኤላውያን በመጀመሪያ ወራቸው በዐሥራ ዐራተኛው ቀን በግ እያረዱ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ፡፡ ሀገራችንም አስቀድማ ብሉይ ኪዳንን የተቀበለች ሀገር እንደመሆኗ ይህ ድርጊት ይፈጸምባት ነበር፡፡ በአንጻሩም ዛሬ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ፋሲካ ተብሎ የተጠራበት ምክንያት በዚህ በፋሲካ በዓል ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጐ ደሙን ስላፈሰሰልን ነው፡፡ በደሙ መፍሰስ ሞተ በኵር የተባለ ሞተ ነፍስ ቀርቶልናልና፡፡ ‹‹ፋሲካችንም ክርስቶስ ነው፡፡›› (1ኛ
ቆሮ.5፤6፣ 1ኛ.ጴጥ.1፤10)
ለ. በዚህ ዕለት እንደ ማክሰኞ ለደቀመዛሙርቱ ረጅም ትምህርት አስተምሯል።
ምሥጢረሥላሴየሦስትነት ትምህርት፤ ምሥጢረሥጋዌ (የአምላክ ሰው መሆን)፤ በዮሐ.14፤16የሚገኘው በጠቅላላ የዚህ ዕለት ትምህርት ነው፡፡ የትምህርቱም ዋና ዋና ክፍሎች ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንና የዳግም ምጽአቱ ነገርነው፡፡
እነዚህም በስፋትና በጥልቀት መማር እንደሚገባ ሲያስረዳን፤በተአምራት ሊገልጥላቸው ሲችል በረጅም ትምህርትእንዲረዱት አድርጓል፡፡ ተማሪዎቹን እሱ እያስተማራቸው ሳለ ያገባቸውን እየጠየቁ ተረድተዋል፡፡ ከዚህም እያንዳንዳችን በቤተክርስቲያን ተገኝተን መማርና ያልገባንን ጠይቆ መረዳት እንደሚገባን እንማራለን፡፡
ሐ.ይህ ዕለት ከደቀመዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ የተባለ ጌታ ሆይ፣ መምህር ሆይ ብሎ በመሳም አሳልፎ የሰጠበት ዕለት ነዉ።