Get Mystery Box with random crypto!

የሰሙነ ሕማማት ሁለተኛ ቀን ሰኞ ፩. መርገመ በለስ (በለስ የተረገመችበት) ዕለት ነው። አንድ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

የሰሙነ ሕማማት ሁለተኛ ቀን
ሰኞ
፩. መርገመ በለስ (በለስ የተረገመችበት) ዕለት ነው።
አንድምታ፡
ወንጌሉ እና ግብረ ሕማማቱ ላይ እንደተገለጸው
☞በለስ የቤተ እስራኤል እና ፍሬ የሃይማኖትና የምግባር ምሳሌ ናቸው ፡፡ ጌታችን ከእስራኤል ፍቅርን፣ ሃይማኖትን፣ ምግባርን ፈለገ፤ አላገኘም፡፡ ስለዚህም እስራኤል ሕዝበ እግዚአብሔር መባልን እንጂ፣ ነቢይነት፣ ካህንነት፣ መሥዋዕት አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፡፡ በመርገሙ ምክንያት ትንቢት ክህነት መሥዋዕት ከቤተ እስራኤል ጠፉ፡፡
☞በለስ ኦሪት ናት፤ ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት "ኦሪትና ነቢያትን ልፈጽም እንጂ ልሽር አልመጣሁም፡፡" በማለት ፈጸማት ፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና ፍሬ ባንቺ አይሁን አላት ፤ ድኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡ በአዲስ ኪዳን የድኅነት ዘመንም ተተካች፡፡
☞በለስ ኃጢአት ናት ፤ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነ ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሰሩት ደስ ያሰኛል ኋላ ግን ያሳዝናል፡፡ "በአንቺ ፍሬ አይገኝ" ማለቱም
"በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር" ማለት ነው፡፡ በለሷም ስትረገም ፈጥና መድረቋ፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በአምላካችን እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡
፪. አንጽሖተ ቤተመቅደስ የተከናወነበት ዕለት ነው።
ጌታችን በለስን ከረገማት በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ ቤተ መቅደስ፣ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምስያጥ (የንግድ ቤት) ሆኖ ቢያገኘው "ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች… እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት" ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው፣ ገርፎም አስወጣቸው...'' እንዲል። (ማቴ ፳፩፡፲፫)
ምስጢሩ :-
☞ቤተመቅደስ የሆንን እኛ የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ አንጽሖተ ቤተመቅደስ የተፈጸመበት ሰኞም በማለት ሊቃውንት ይገልጹታል።
@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox