Get Mystery Box with random crypto!

መስከረም ፲ ጼዴንያ ማርያም ጼዴንያ በምትባል ሀገር ማርታ የምትባል ደግ ሴት ነበረች፡፡ ይህች ደ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

መስከረም ፲
ጼዴንያ ማርያም


ጼዴንያ በምትባል ሀገር ማርታ የምትባል ደግ ሴት ነበረች፡፡ ይህች ደግ ሴት በቤቷ ትልቅ አዳራሽ ሠርታ እንግዶችን እንደ አባታችን አብርሃም ተቀብላ አብለታ አጠጥታ ማደሪያ ቦታም ሰጥታ ታስተናግድ ነበር፡፡ አባ ቴዎድሮስ የሚባል ኢትዮጵያዊ መነኩሴ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ መሽቶበት ከማርታ ቤት በእንግድነት አደረና ጠዋት ሊሄድ ሲነሣ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ሲነግራት ‹‹የእመቤታችንን ሥዕል ገዝተህ አምጣልኝ ዋጋውን ልስጥህ›› አለችው፡፡ እርሱም ‹‹ገንዘቡን ሥዕሉን ሳመጣልሽ ትሰጪኛለሽ›› ብሏት ሄደ፡፡ ኢየሩሳሌምም ደርሶ ቅዱሳት መካናትን ተሳልሞ ሥዕሉን ረስቶ ሳይገዛ ሲመለስ «አደራ ጥብቅ አይደለምን? ያቺ ሴት አደራ ያለችህን ለምን ረሳህ» የሚል ድምፅ ሰማ፡፡ በጣም ደንግጦ ተመልሶ ሄዶ ገዝቶ በረሃ በረሃውን መጓዝ ጀመረ፡፡ በመንገድም እየተጓዘ አንበሳ ሊበላው እየሮጠ ወደ እርሱ ሲመጣበት አየ፡፡ መነኩሴው አንበሳውን ከመፍራት የተነሣ ደነገጠ፣ ተንቀጠቀጠ ደንግጦ ቁሞ ሳለ ያች ሥዕል ከአንበሳው ጩኸት ሰባት እጅ በሚበልጥ አስፈሪ ድምፅ ጩሃ ተናገረች፡፡ ያን ጊዜ አንበሳው ደንግጦ ፈጥኖ ሸሸ፡፡ መነኩሴውም መንገዱን ቀጠለ፡፡ በመንገዱም ከሚያስፈራ ዱር ውስጥ ወጥተው ወንበዴዎች ሊቀሙትና ሊገድሉት ከበቡት፡፡ ከሥዕለ ማርያሟም እንደ መብረቅ ያለ ታላቅ ቃል ወጣ፡፡
ወንበዴዎችም እጅግ ፈርተው ሸሽተው ከጫካው ውስጥ ገቡ፡፡ ያም መነኩሴ እነኚህን የሚያስደንቁ ተአምራት በተመለከተ ጊዜ በልቡ «ለእኔ ረዳት ትሆነኝ ዘንድ ወደ ሀገሬ ይዣት እሄዳለሁ እንጂ ለላከችኝ ሴት አልሰጥም» ብሎ ወደ ሀገሩ ሊሄድ በመርከብ ተሳፈረ፡፡ በባሕር ላይም ሳለ ጽኑ ነፋስ ተነስቶ መርከቡን እየገፋ ማርታ ወዳለችበት ሀገር ወደ ጽዴንያ ዳርቻ አደረሰው፡፡ ማደሪያም ስለሌለው ወደ ደጓ ሴት ወደ ማርታ ቤት ከእንግዶች ጋር አብሮ ገብቶ አደረ፡፡ ሲነጋ ወጥቶ ሊሄድ ከደጃፍ ሲደርስ ደጃፉ ጠፍቶት ከአጥሩ ሲታገል ዋለ፡፡ ማርታም «አባቴ ያመመህ የደከመህ ትመስላለህ ዛሬ ደግሞ እዚህ እደርና ነገ ትሄዳለህ» አለችውና አደረ፡፡ በሁለኛውም ዕለት እንደ መጀመሪያው ቀን በሩን አልፎ መሄድ አቃተውና እዚያው ማርታ ቤት አደረ፡፡ በሦስተኛው ቀን መውጣት ፈልጐ አሁንም ከአጥሩ ጋር ሲታገል አይታ «አባቴ የሆንከው ምንድነው? እነሆ ዛሬ ሦስተኛ ቀንህ ነው» አለችው፡፡
መነኩሴውም «ይህችን ተአምረኛ ሥዕል አልሰጥም ብዬ ነው፡፡ እኔኮ ሥዕል ከኢየሩሳሌም ግዛልኝ ያልሽኝ መነኩሴ ነኝ» ብሎ ሥዕለ ማርያምን አውጥቶ ሰጣት፡፡ እርሷም እጅግ በጣም ተደስታ እግዚአብሔርን አመሰገነች፡፡ በሥዕሏም ፊት ሰግዳ ለእመቤታችን ለድንግል ማርያም ምስጋናን አቀረበች፡፡ ተቀብላም ሥዕል ቤት አሠርታ በክብር አስቀመጠቻት፡፡ ይህችም ሥዕል ቅዱስ ሉቃስ የሳላት ናት፡፡ ሥጋ የለበሰች ትመስላለች፡፡ ከፊቷም ወዝ ይንጠባጠባል፡፡ በዚህችም ሥዕል ብዙ ተአምራት ተደረገ ሕሙማን ተፈወሱ፣ ዐይነ ስውራን ማየት ቻሉ፡፡ በዚያ ዘመን የነበረው ሊቀ ጳጳስ ተአምሯን ሰምቶ ሥዕሏ ወደ ማርታ ቤት የገባችበት ዕለት መስከረም ፲ ቀን እንዲከበር ሥርዓት ሠራ፡፡ ይህም በዓል በቤተ ክርስቲያናችን ሁልጊዜ ይከበራል፡፡
የብርሃን እናቱ ድንግል ወላዲተ አምላክ ፍቅሯን ጣዕሟን ታሳድርብን፣ ልጇ አምላካችን በጸሎቷ ይማረን!

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox