Get Mystery Box with random crypto!

መስከረም ፪ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ መስከረም ሁለት በዚህች ቀን የካህኑ የዘካርያስ ልጅ የከበረ አ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

መስከረም ፪
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ

መስከረም ሁለት በዚህች ቀን የካህኑ የዘካርያስ ልጅ የከበረ አጥማቂው ዮሐንስ ሕግን አፍራሽ በሆነ በንጉሥ ሄሮድስ እጅ ሰማዕት ሆነ።

ይህም እንዲህ ነው በፊልጶስ ሚስት በሄሮድያዳ ምክንያት ነቢዩ ዮሐንስ በገሠጸው ጊዜ ፊልጶስ ወንድሙ ስለሆነ ቅዱስ ዮሐንስም የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም ይለው ነበርና።

ቅዱስ ዮሐንስም ሄሮድስን የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን ስለማግባቱና ሌላም ያደርገው ስለነበረ ክፉ ሥራ ሁሉ ይገሥጸው ነበር። ደግሞም በተግሣጽ ላይ ተግሣጽን ጨመረ። ስለዚህም ዮሐንስን ተቀየመውና በግዞት ቤት አኖረው።

ሄሮድስም ዮሐንስን ይፈራው ነበር ጻድቅ ቅዱስ ሰው እንደሆነ ያውቅ ነበርና ብዙ ይጠባበቀውም ነበር። ሄሮድስ የተወለደባትን ቀን በዓል የሚያከብርባት ዕለት ነበረች መኳንንቱን አለቆቹን መሣፍንቱን ሹሞቹን በገሊላ አገር ያሉትን ታላላቅ ሰዎች ግብር አገባ።

የሄሮድያዳ ልጅም ወደ አዳራሹ ገብታ ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው ከእርሱ ጋር በማዕድ የነበሩትንም ንጉሡም ያቺን ብላቴና የምትሺውን ለምኚኝ እሰጥሻለሁ አላት። እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስም ቢሆን የለመነችውን ሊሰጣት ማለላት።

ወጥታም እናቷን ምን ልለምነው አለቻት እናቷም የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አለቻት። ያን ጊዜም እየሮጠች ወደ ንጉሡ ገብታ የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ በወጭት አሁን እንድትሰጠኝ እሻለሁ ብላ ለመነችው። ንጉሡም ስለ መሐላው አብረውት ስለ ነበሩትም ሰዎች አዘነ እምቢ ሊላት ግን አልወደደም።

ያን ጊዜም ባለወጎችን ላከ በእሥር ቤትም ሳለ የዮሐንስን ራስ ቆረጡ ራሱንም በወጭት አምጥተው ለዚያች ብላቴና ሰጡአት እርሷም ወስዳ ለእናቷ ሰጠች። በዚያችም ቀን የቅዱስ ዮሐንስ ራስ ከሄሮድያዳ ከእጆቿ ላይ ወደ አየር ስለ በረረች ታላቅ ድንጋፄ ሆነ።

ደግሞም ሄሮድስ ሆይ የወንድምህን ሚስት ልታገባ አይገባህም እያለች በመጮኽ ዘልፋዋለችና። ደቀ መዛሙርቱም በሰሙ ጊዜ መጥተው በድኑን ወስደው ቀበሩት።

ስንክሳር

@Ethiopian_Orthodox
@Ethiopian_Orthodox