Get Mystery Box with random crypto!

ነሐሴ ፲፫ ደብረ ታቦር ደብረ ታቦር በቁሙ እሥራኤል ውስጥ ከሚገኙ ተራሮች አንዱ ነው:: ተራራው | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ነሐሴ ፲፫
ደብረ ታቦር

ደብረ ታቦር በቁሙ እሥራኤል ውስጥ ከሚገኙ ተራሮች አንዱ ነው:: ተራራው ብዙ ታሪካዊ ዳራዎች ቢኖሩትም ክብሩ ከፍ ከፍ ያለው ግን ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን ስለ ገለጸበት ነው:: ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

+አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋችንን በተዋሐደባት በዚያች በተወደደች ጊዜ: ደቀ መዛሙርቱ ስለ እግዚአብሔር መንግስት ምሥጢርን ይማሩ ነበር:: በጊዜው ግን አበው ሐዋርያት ምሥጢር ባይገባቸው: አንድም ገና መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ አልወረደም ነበርና እምነታቸው ሙሉ አልነበረም::

+ጌታም አምላክነቱን በየጊዜው በቃልም: በተግባርም ይገልጥላቸው ነበር:: በርግጥ ያንን ነደ እሳት: ሰማያት የማይቸሉትን ግሩማዊ አምላክ በትሑት ሰብዕና መመልከቱ ሊከብድ እንደሚችል መገመት አያዳግትም::

+ጌታችን ብዙ ተአምራትን በአምላካዊ ጥበቡ ሠርቷል:: እጅግ ድንቅ ከሆኑት መካከል ደግሞ ቅድሚያውን ደብረ ታቦር ይይዛል:: ጌታ ስለ ምን መለኮታዊ ክብሩን በደብረ ታቦር ገለጸ ቢሉ:-
1.ትንቢቱ ሊፈጸም (መዝ. 88:12)
2.ምሳሌው ሊፈጸም (ባርቅና ዲቦራ በሢሣራ ላይ ድልን ተቀዳጅተዋልና)
3.ሊቀ ነቢያት ሙሴ "ልይህ" ብሎ ከ1,500 ዓመታት በፊት ጠይቆ ነበርና እርሱን ለመፈጸም
4.አንድነቱን: ሦስትነቱን ለመግለጽ
5.ቤተ ክርስቲያንን በምሳሌ ለማሳየት
6.ተራራውን ለመቀደስ
7.የሐዋርያቱን ልብ ለማጽናት . . . ወዘተ ነው::

+ነሐሴ 7 ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ቂሣርያ ፊልዾስ ወስዶ "የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?" ብሎ ጠይቁዋቸው ነበር:: እነርሱም የራሳቸውን ሐሳብ የሌላ እያስመሰሉ "አንዳንዶቹ ኤልያስ: አንዳንዶቹም ሙሴ: ሌሎቹም ከነቢያት አንዱ ነው ይሉሃል" አሉት::

+ኩላሊትን የሚመረምር ፈጣሪ ነውና "እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?" ቢላቸው ደንግጠው ዝም አሉ:: የሃይማኖት አባት: ባለ በጐ ሽምግልና ቅዱስ ዼጥሮስ ግን በመካከላቸው ቆሞ "አንተ ውዕቱ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ሕያው - የሕያው እግዚአብሔር አንድያ የባሕርይ ልጁ ክርስቶስ አንተ ነህ" አለው:: በዚያን ጊዜ ቃለ-ብጽዓን እና የመንግስተ ሰማያት መክፈቻ ተሰጠው:: (ማቴ. 16:13)

+መጽሐፍ እንደሚል ደግሞ እንዲህ ከሆነ ከ6ኛው ቀን በሁዋላ ጌታችን 12ቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ደብረ ታቦር ወሰዳቸው:: ዘጠኙን በእግረ ደብር (ከተራራው ሥር) ትቶ 3ቱን (ዼጥሮስን: ዮሐንስንና ያዕቆብን) ይዟቸው ወጣ:: እኒሕ ሐዋርያት "አዕማድ: አርዕስት: ሐዋርያተ ምሥጢርም" ይባላሉ::

+በተራራው ላይ ሳሉም ድንገት የጌታችን መልኩ ከፀሐይ 7 እጅ አበራ: ከመብረቅም 7 እጅ አበረቀ:: "ወኮነ ልብሱ ጸዐዳ ከመ በረድ" እንዲል ከታቦር የተነሳው ብርሃነ ገጹ አርሞንኤም ደርሷል:: ያንን ተመልክተው መቆም ያልቻሉት ሐዋርያቱ ፈጥነው መሬት ላይ እንደ ሻሽ ተነጠፉ::

+በዚያች ሰዓት ሙሴ ከመቃብር: ኤልያስም ከብሔረ ሕያዋን መጡ:: አንዳንዶቹ ጌታን 'ነቢይ' (ሎቱ ስብሐት) ብለውታልና ሙሴና ኤልያስ ተናገሩ:- "ስለ ምን አንተን ነቢይ ይሉሃል: እግዚአ ነቢያት - የነቢያት ፈጣሪ ነህ እንጂ" እያሉ ተገዙለት: አመሰገኑት::

+ነገር ግን በቦታው ጸንተው መቆየት አልቻሉም:: መለኮታዊ ብርሃኑ ቢበዘብዛቸው ቅዱስ ሙሴም ወደ መቃብሩ: ቅዱስ ኤልያስም ወደ ማደሪያው በድንጋጤ ሩጠዋል::

+በዚያች ሰዓት ሊቀ ሐዋርያት ጌታን "ሠናይ ለነ ኀልዎ ዝየ: ንግበር ሠለስተ ማሕደረ: አሐደ ለከ: ወአሐደ ለሙሴ: ወአሐደ ለኤልያስ - ጌታ ሆይ! በዚህ መኖር ለኛ መልካም ነው:: በዚህም 3 ዳስ እንሥራ:: አንዱን ላንተ: አንዱንም ለሙሴ: አንዱን ለኤልያስ" ብሎታል::

+ቅዱስ ዼጥሮስ ለራሱ ሳያስብ ለጌታና ለቅዱሳን ነቢያቱ "ቤት እንሥራ" በማለቱ ሲመሰገን ጌታን የመጣበትን የማዳን ሥራ የሚያስተው ጥያቄ በማቅረቡ ከድካም ተቆጥሮበታል:: ለሁሉም ግን ሐሳቡ ድንቅና መንፈሳዊ ነው::

+እርሱ ይሕንን ሲናገር መንፈስ ቅዱስ በደመና አምሳል ወረደና ከበባቸው:: አብ ከሰማይ ሆኖ "ዝንቱ ውዕቱ ወልድየ ዘአፈቅር: ወሎቱ ስምዕዎ - የምወደው: የምወልደው: ሕልው ሆኘ የምመለክበት የባሕርይ ልጄ እርሱ ነውና ስሙት" ሲል ተናገረ::

+ደቀ መዛሙርቱም ከፍርሃት የተነሳ በዚያች ሰዓት እንደ በድን ሁነው ነበርና ጌታችን ቀርቦ ቀሰቀሳቸው:: በተነሱ ጊዜ ግን ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት ተመልሶ ነበር:: (ማቴ. ማር. ሉቃ. )

+በደብረ ታቦር የጌታችን ብርሃነ መለኮት ያዩ 3ቱ ሐዋርያት ብቻ አይደሉም:: እመ ብርሃን ካለችበት ሆና ስትመለከት 12ቱ ሐዋርያት ደግሞ በተራራው ሥር ሆነው በተደሞ ተመልክተዋል::

+ይሕንን ድንቅ ብርሃነ መለኮት ያላየ ይሁዳ ብቻ ሲሆን እርሱም ስለ ክፋቱ የኢሳይያስ ትንቢት ተፈጽሞበታል:: ኃጢአተኛው የእግዚአብሔርን ክብር እንደማያይ ተነግሮበታልና:: "ያአትትዎ ለኃጥእ ከመ ኢይርዐይ ስብሐተ እግዚአብሔር" እንዲል:: (ኢሳ.)
ሊቁም የደብረ ታቦርን ምሥጢር ሲያደንቅ እንዲህ ብሏል:-

"ጸርሐ አብ ኪያከ በውዳሴ:
ወበርእስከ ጸለለ መንፈሰ ቅዳሴ:
አመ ገበርከ እግዚኦ በታቦር ምስለ ሐዋርያት ክናሴ:
መንገለ ሀሎ ኤልያስ ወኀበ ሐለወ ሙሴ:
ዘመለኮትከ ወልድ ከሠትከ ሥላሴ::"

ማቴ. ፲፯፡፩-፭ በቤተ ክርስቲያን ደብረታቦር ከቤተክርስቲያን ውጭ አከባበሩ ቡሄ እየተባለ የሚከበረው በዓል በሀገራችን በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡ ቡሄ ማለት ብራ፣ ብርሃን፣ ደማቅ ገላጣ፣ የተገለጠ ማለት ነው፡፡ ቡሄ ሲመጣ የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ወደ ብርሃን፣ ወደ ጥቢ የሚያመራበት፣ ወደ መፀው የሚዘለቅበት ወገግታ ፣ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት፣ የሚሸጋገርበት ወቅት በመሆኑ ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምት አይኖርም፡፡ በዚህ መሰረት የክረምቱ አፈና ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታየውም በዚህ በዓል አካባቢ ስለሆነ ይቺ ዕለት 'ቡሄ' የሚለውን ስያሜ አገኘ። ቡሄ ማለት ገላጣ፣ የተገለጠ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት፣ ብረሃን የታየበት ድምጸ መለኮት የተሰማበት ስለሆነ፤ ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል በማለት የቡሄ በዓልም ይባላል፡፡

በገጠርም ሆነ በየከተማው ልጆች ጅራፋቸውን ገምደው ሲያጮሁ ይሰነብታሉ። እናቶችም ለበዓሉ ዝግጅት ስንዴ ሲለቅሙ፣ ሲፈትጉ፣ ሲፈጩ ይሰነብታሉ። መነሻ የሆናቸው ትውፊት ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ዕለት ጊዜው ምሽት ነበር፡፡ እረኞችም ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል ፡፡ያንን ለማስታወስ «ቡሄ» ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና ችቦ በማብራት በዓሉን የሚከበረው ከዚህ በመነሣት ነው፡፡
የንጋት ወጋገን ሲፈናጠቅ ልጆች በከባድ ድምጽና በጅራፍ ጩኸት የሚታጀብ፣ በገደላገደል ስር እንዲያስተጋባ ተደርጎ ብዛት ባላቸው ህጻናት በከፍተኛ ድምጽ የሚዘመር ነው ቡሄ። የጅራፉ ጩኸትም እግዚአብሔር አብ “የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” ሲል ሐዋርያት ራሳቸውን ስተው የወደቁበትን የመለኮት ድምፅ ለማስታወስ ነው፡፡