Get Mystery Box with random crypto!

ችንም አነሣችውና ‹‹ሳትጠይቀኝ መጽሐፌን ትጽፍ ዘንድ ለምን ደፈርህ?›› አለችው፡፡ ‹‹እኔ ወድጄህ | የኦርቶዶክስ አስተምህሮዎች

ችንም አነሣችውና ‹‹ሳትጠይቀኝ መጽሐፌን ትጽፍ ዘንድ ለምን ደፈርህ?›› አለችው፡፡ ‹‹እኔ ወድጄህ ከእናትህስ ማኅፀን መርጬህ ለጴጥሮስ፣ ለጳውሎስና ለዮሐንስ አደራ ሰጥቼህ የለምን?›› አለችው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ‹‹እመቤቴ ሆይ ይቅር በይኝ፣ ደስ የሚያሰኝሽ መስሎኝ ይህን ባለማወቅ ሠርቼዋለሁና›› አላት፡፡ እመቤታችንም ‹‹ወዳጄ ሆይ ይቅር ብየሃለሁ›› አለችው፡፡ ‹‹ልትጽፈው የወደድኸው መጽሐፍም እነሆ በእጄ አለ፣ ከአሁን በኋላ የተወደደ ልጄ በአንደበትህ ሊገልጸው ወዷል፡፡ ነገር ግን ከአርያም ከሰማይ ኀይልን እስክትለብስ ድረስ አትቸኩል፡፡›› ይህንም ብላው ከእርሱ ተሰወረች፡፡ ያን ጊዜም ልቡ እንደ ፀሐይ በራ፣ የመለኮትም ባሕር በኅሊናው አበራ፡፡ በመንፈስ ቅዱስም መስተዋትነት የተሰወረውን ሁሉ አየ፡፡

የመጀመርያው ድርሰቱ አርጋኖን የተሰኘውና በቅኔ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚያመሰግነው መጽሐፉ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በሚወድ በንጉሥ ዳዊት ዘመንም አርጋኖን መጽሐፍን ይደርስና ይጽፍ ጀመረ፡፡ በሦስትም ስሞች ጠራው እነዚህም አርጋኖና ውዳሴ፣ መሰንቆ መዝሙር፣ ዕንዚራ ስብሐት ናቸው፡፡ ስለ መጽሐፉም ጣፋጭነት ንጉሡ ዐፄ ዳዊት ድርሰቱን በጣም ከመውደዱ የተነሣ በወርቅ ቀለም አጻፈው፡፡ ወርቁን የሚያንጸባርቅበት ድንጋይ (ዕንቊ) ባጣ ጊዜ እመቤታችን ማርያም በሌሊት ራእይ ዘማት በሚባል አገር እንዳለ ለጊዮርጊስ ነገረችው ኅብሩንም አሳየችው፡፡ አባታችን ጊዮርጊስም ከደረስኳቸውና ከተናገርኋቸው ድርሳናት ሁሉ አርጋኖን ውዳሴ ይጣፍጣል ይበልጣል አለ፡፡

‹‹እንደዚሁም በፈጣሪው ቸርነት በእመቤታችን ረድኤት ብዙ ድርሳናትንና የጸሎት መጻሕፍትን ደረሰ፡፡ የእሊህም ድርሳናት ስማቸውና ቁጥራቸው በሊቃውንት ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ እሊህም ውዳሴ መስቀል፣ መጽሐፈ ብርሃን፣ መጽሐፈ ሰዓታት የመዓልትና የሌሊት፣ መጻሕፍተ ቅዳሴያት ናቸው፡፡ ጸሎተ ፈትቶ (የፍታቴ ጸሎት) የሐዋርያት ማኅሌት፣ መልክአ ቊርባን፣ እንዚራ ስብሐት፣ አርጋኖን ውዳሴ፣ ፍካሬ ሃይማኖት፣ ውዳሴ ሐዋርያት፣ ኖኅተ ብርሃን ይኸውም ከመጽሐፈ አርጋኖን ጋር አብሮ የታተመው ነው፡፡ ፍካሬ ሃይማኖት፣ መጽሐፈ ምስጢር፣ ሕይወታ ለማርያም፣ ተአምኆ ቅዱሳን፣ ጸሎት ዘቤት ውስተቤት፣ ውዳሴ ስብሐት፣ ሰላምታ፣ ጸሎተ ማዕድ፣ ቅዳሴ እግዚእ ካልእ፣ መዝሙረ ድንግልና የመሳሰለው ነው፡፡›› ቅዱስ ገድሉ እንደሚናገረው የአባ ጊዮርጊስ ‹‹ድርሳናት ስማቸውና ቁጥራቸው በሊቃውንት ዘንድ የታወቀ ነው›› ብሎ ከጀመረ በኋላ በቁጥር የተወሰኑትን ድርሰቶቹን ብቻ ጠቅሶ መጨረሻ ላይ ‹‹… እና የመሳሰለው ነው›› ብሎ ይደመድመዋል፡፡ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ደግሞ የአባ ጊዮርጊስ ድርሰቶች ከ12 ሺህ በላይ ቢሆኑም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እየሰጡ ያሉት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸውን በቅዱሳን ታሪክ መጽሐፋቸው ላይ ጠቅሰውታል፡፡ ሌሎች ሊቃውንት አባቶቻችንም የአባ ጊዮርጊስን ድርሰቶች ከግምት ባለፈ ሁኔታ በቁጥር ወስኖ ለማስቀመጥ አስቸጋሪ መሆኑን ይገልጣሉ፡፡ ይኸውም ወደፊት ራሱን የቻለ በቂና ብዙ ጥናት ማድረግ ሳያስፈልገን እንደማይቀር አመላካች ነው፡፡

የመጀመርያውን ድርሰቱን አርጋኖንን እመቤታችን አብዝታ ስለወደደችለት ዚማት በሚባለው ሀገር በነበረ ጊዜ ‹‹ከድርሰቶችህ ሁሉ እንደ አርጋኖን የምወደው የለም›› ብላዋለች፡፡ ከዚህ በኋላ የደረሰው ድርሰት ውዳሴ መስቀል ይባላል፡፡ ቀጥሎም መጽሐፈ ስብሐት ዘመዓልት ወዘሌሊት የተባለውን ወይም እርሱ ራሱ መጽሐፈ ብርሃን ብሎ የሰየመውን መጽሐፍ አዘጋጅቷል፡፡ መጽሐፉም የእግዚአብሔርን የምስጋናውን መንገድ ያበራል፣ አብርቶ ያመለክታልና፣ ልዑላነ ብርሃን የሆኑትን የማኅበረ ቅዱሳንንና የትጉኃንን የምስጋናቸውን መንገድ ያመለክታልና፣ የእመቤታችንንም የምስጋናዋን ጣዕም ይገልጣልና መጽሐፉ «መጽሐፈ ብርሃን» ተባለ፡፡ በዘመኑ በነበረው ልማድ ካህናቱ ቍርባን በሚያቀብሉ ጊዜ ሕዝቡ ወደ ካህናቱ መጥተው ሲቀበሉ ንግሥቲቱ ግን ካለችበት ድረስ ካህናቱ ሄደው ነበር የሚያቆርቧት፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን ‹‹ይህ ቁርባን ንጉሠ ነገሥት ነውና ንግሥቲቱ ወደዚህ መጥታ ልትቀበል ይገባታል እንጂ እኛ መሄድ የለብንም›› ሲል ተቃወመ፡፡ ይህ ነገር ንግሥቲቱንና አባ ጊዮርጊስን ስላጋጫቸው ዐፄ ዳዊት ችግሩን ለመፍታት አባ ጊዮርጊስን ወደ ሀገረ ዳሞት ንቡረ እድነት ሾሞ ላከው፡፡

ከዚህ በኋላ አባ ጊዮርጊስ ዋናው ትኩረቱ በድርሰቱ ላይ በማድረግ ወደ ጳጳሱ ወደ አቡነ በርተሎሜዎስ ዘንድ በመሄድ የቅዳሴ ድርሰት ለመድረስ እንዲፈቀድለት ጠይቆ ሲፈቀድለት የቅዳሴ ድርሰት ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ነገረ ሃይማኖትን ጠንቅቆ የተረዳና የሚያስረዳ ስለነበር በዘመኑ የተነሡ የሃይማኖት ክርክሮች ሁሉ እርሱ ከሌለ አይሳኩም ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ በሸዋ በይፋት ራሳቸውን ቤተ እስራኤል እያሉ የሚጠሩ አይሁድ ነበሩ፡፡ ከአቡነ ዜና ማርቆስ ጀምሮ ብዙ መምህራን ወደነዚህ ሕዝቦች እየተሠማሩ ወንጌልን አስተምረዋል፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ክርስትና ለተመለሱት ቤተ እስራኤላውያን በእመቤታችን፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በአባ ኖብና በሰማዕቱ በጊጋር ስም አራት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተው ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ቤተ እስራኤላውያኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ክርስትና አልተመለሱም ነበር፡፡ ከእነዚህ አይሁድ መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ፡፡ ‹‹ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደነርሱ ሃይማኖት እገባለሁ እኔ ከረታኋቸውም ወደኔ ሃይማኖት ይገባሉ›› ሲል ነገሩን ጥብቅ አደረገው፡፡ ዐፄ ዳዊት ይህን ጉዳይ ሲሰማ በጣም ስለ ተናደደ ሊቃነ ካህናቱን፣ ንቡራነ እዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር፡፡ አይሁዳዊው በአንድ ወገን መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን ጀመሩ፡፡ የመጀመርያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አቀረበ፡- ‹‹እናንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉት ይሄ ክርስቶስ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፣ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ ‹አልዓዛርን የት ቀበራችሁት?› ብሎ እንደ ጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ስጡኝ፣ እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪቴ ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ?›› ሲል የመከራከርያ ነጥቡን አቀረበ፡፡ ሊቃውንቱም በዚህ ጊዜ ታሞ አልጋ ላይ የነበረውን አባ ጊዮርጊስን እንዲመጣላቸው ፈልገው ‹‹እንዲህ ያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ›› ሲሉ ለዐፄ ዳዊት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደርጎ በአልጋ ላይ ሆኖ በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ ጉባኤተኞቹ የቀረበውን ጥያቄ በነገሩት ጊዜ አባ ጊዮርጊስ የሰጠውን መልስ እንዲህ የሚል ነው፡- ‹‹እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ፡፡ የምኩራብ መጻሕፍት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና፡፡ ምኩራብ ዘራች ቤተ ክርስቲያንም አጨደችው፤ ምኩራብ ፈተለችው ቤተ ክርስቲያን ለበሰችው፤ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ ወዴት ነህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? አብርሃምንስ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? ብሎ የጠየቀው ማነው? እስቲ መልስልኝ? ሰይጣንንስ ከወዴት መጣህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? እግዚአብሔር አብ አይደለምን?›› እያሉ የጥያቄ ዓይነት ባሽጎደጎዱለት ጊዜ አይሁዳዊው መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡ መልስ በማጣቱም አፈረ፡፡ ንጉሡ፣ ሊቃውንቱና መኳንንቱም እጅግ ተደሰቱ፡፡

አባ ጊዮርጊስ ሌላው ያጋጠመው ክርክር ቢቱ ከተባለው