Get Mystery Box with random crypto!

ዐበይት ዜናዎች 1፤ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስት | 💚💛❤️ ዮቶራዊያን💚💛❤️

ዐበይት ዜናዎች

1፤ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ኢትዮጵያን ሊጎበኙ መሆኑን ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ማስታወቃቸውን መግለጫውን የተከታተሉ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ብሊንከን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው፣ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። ብሊንከን መቼ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ግን መለስ አልጠቀሱም። ብሊንከን ኢትዮጵያን ከጎበኙ፣ የሰሜኑ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የአሁኑ ጉብኝታቸው የመጀመሪያቸው ይሆናል።

2፤ በኦሮሚያ ክልል የጉጂ ዞን የአገር ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች አዲስ በተዋቀረው ምሥራቅ ጉጂ ዞን ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለፌደራሉና ለክልሉ መንግሥት ማቅረባቸውን ትናንት አዲስ አበባ ላይ በሰጡት መግለጫ መናገራቸውን የዋዜማ ሪፖርተር ዘግቧል። የአገር ሽማግሌዎቹ፣ የክልሉ መንግሥት የአዲሱን የምሥራቅ ቦረና ዞን ስያሜ እለውጣለሁ ማለቱን ሽማግሌዎቹ ተናግረዋል። አዲሱ ምሥራቅ ቦረና ዞን በቅርቡ የተደራጀው፣ ከቦረና፣ ጉጂ እና ባሌ ዞኖች አንዳንድ ቦታዎችን በማካተት ሲሆን፣ ሦስቱ ዞኖች ተመካክረው የዞኑ ስያሜ እንደሚቀየር እንደተነገራቸው የአገር ሽማግሌዎቹ ገልጸዋል። የጉጂ ዞን ዋና ከተማ ነገሌ ቦረና በአዲሱ ዞን ስር መካለሏንና ጉጂ ዞን ዋና ከተማውን አዶላ ሬዴ ላይ እንዲያደርግ የተወሰነውን ውሳኔ በመቃወም፣ በጉጂ ዞን የተቃውሞ ሰልፎችን ሲያደርጉ ሰንብተዋል።

3፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋ የመኖሪያ ቤት አከራዮች እስከ መጭው ሰኔ ወር ድረስ የቤት ኪራይ እንዳይጨምሩ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል። የከተማዋ አስተዳደር፣ በከተማዋ የተከሰተውን የኑሮ ውድነትና ከፍተኛ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር በአስቸኳይ የእህል ምርት ወደ ከተማዋ በብዛት እንዲገባና እንዲሰራጭ የሚያስተባብር ግብረ ኃይል ማቋቋሙንም ገልጧል።

4፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በሱዳን ዳርፉር ግዛትላይ የጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ለአንድ ዓመት አራዝሟል። ጸጥታው ምክር ቤት፣ ለዳርፉር ያቋቋመው የባለሙያዎች ተቆጣጣሪ ቡድን የሥራ ቆይታ ጭምር እንዲራዘም ወስኗል። ሆኖም ምክር ቤቱ ከቀነ ገደቡ በፊት ሁኔታዎችን እየገመገመ ማዕቀቡን ሊያሻሽል እንደሚችል ገልጧል። የሱዳን ወታደራዊ መሪዎች፣ ጸጥታው ምክር ቤት የጦር መሳሪያ ማዕቀቡን እንዲያነሳ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። [ዋዜማ]