Get Mystery Box with random crypto!

ያለፈ ጥረታችንን ሳስታውስ ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ። ሃገር ስትታመም፣ ብ | ስብዕናችን #Humanity

ያለፈ ጥረታችንን ሳስታውስ ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ። ሃገር ስትታመም፣ ብርድ ብርድ ሲላት፣ ተስፋና ሥጋት፣ ወኔና ፍርሃት፣ ምርቃትና እርግማን - እንዳሻው ሲንጣት ከሆነብን ይልቅ እየሆነ ያለው ያሳስበኛል ፣ ከእሳቱ በላይ አያያዙ ያሰጋኛል፣ ከጥያቄው በላይ ምላሹ ይስበኛል።

ችግር ፈቺነት ከሚጠይቀው ጥበብ ውስጥ ዋነኛው የሚመስለኝ ለሌላ እንከን ገርበብ የማይልን በር የመተው ብልህነት ነው። አንድን ሕመም ስታክም 'ከተጠባቂው' ጎንዮሽ እንከን ውጭ ሌላ ህመም እንዳልፈጠርክ ማረጋገጥ ግዴታህ ነው። በስመ መድኃኒት የተገኘው አይደነጎርም፣ አንድ ችግር ፈትቷል ተብሎ ለሌሎች ችግሮች ሰበብ እንዲሆን አይተውም፣ በእውቀት እንጂ በደመነፍስ አይቃኝም።

በእንዲህ ዓይነት ጊዜ ጥሞና ነው የሚያስፈልገን፣ የሰከነ ውይይት ነው የሚያሻን፣ 'ምን ብናደርግ ይበጃል?' መባባል አለብን። ጊዜው እሾህ እያወጣን ጦር የምንተክልበት አይደለም፣ እንቅፋት እየነቀልን ፈንጂ የምንቀብርበት አይደለም፣ ጀግነን አዙሪቱን እኛው ጋ የምናቆምበት እንጂ፣ የክብሪቱን እሳት እፍ በምትልበት ሰዓት ካላጠፋኸው እፍ ብሎ ያጠፋሃል።

'ካልደፈረሰ አይጠራም' የሚል አስተሳሰብ የሚያቀነቅኑ ሰዎች ዛሬም በዙሪያችን እንዳሉ ማሰብ ያደክማል፣ ሳይደፈርስ ማጥራት ከተቻለ ለምን ይደፍርስ ብሎ መጠየቅ ግን ግድ ነው። የደፈረሰ ሁሉ ይጠራል ወይ ማለትም ያስፈልጋል፣ ድፍርስ ሲጠራ ዝቃጭ እንደሚተው አለመርሳትም ደግ ነገር ነው። ምንም ብንታገል ልናስቀር የማንችለው አንድ ነገር ለውጥ ብቻ ነው፣ ለበጎ አልያም ለክፉ እንዲሆን የማድረጉ ድርሻ ግን እጃችን ላይ አለ። ችግሩ 'እንዲሆን' የምንፈልገው አለ - ሆነን ግን አንጠብቀውም.. 'እንዲመጣ' የምንሻው አለ - የምናዋጣው ግን የማይገባውን ነው።

በእንዲህ ያለ ቀውጢ ጊዜ ወሳኙ ሰው አንተ ነህ፣ ዘረኛ ሳይሆኑ ነው ዘረኝነትን ማረቅ የሚቻለው፣ ሳይሰርቁ ነው ዘራፊነትን ማስቆም የሚቻለው፣ አድማጭ ሆኖ ነው ጫጫታን ማስቆም የሚቻለው፣ ግማሽ መንገድ መጥቶ ነው 'እስኪ እንነጋገር' የሚባለው፣ለውጡን ተለወጠው እንጂ ከሌሎች አትጠብቀው፣ አርዓያ ሁን የሚመለከቱህ አሉ ፣ የሚከተሉህ አሉ።

ፊት መሆን በሚችል ስብዕና ከፊት ቁም፣ ጊዜህን አፍ በመካፈት አትብላው፣ ስህተት በመንቀስ አትሙላው ብሽሽቁ፣ አተካራው፣ መናቆሩ፣ ጎራ ማበጀቱ ፣ አሁን ፈጽሞ አይጠቅምም። እንዲመጣ የምትፈልገው ለውጥ አሁን አንተ ያልሆንከው ወይም የሌለህ ከሆነ ለውጡ መቼም አይመጣም መቼም!!

የትኛውም የችግር ቁልፍ የፍቅር ስሪት ከሌለው መሰበሩ አይቀርም ፣ ወደድክም ጠላህ እውነተኛውና ዘላቂው ኃይል ፍቅር ብቻ ነው ፣ የረቀቀ ሳይንስም ሆነ የጠለቀ አስተሳሰብ ፍቅርህን አያክልም፣ የገዘፈ ኃይልም ሆነ ልክ የለሽ ስልጣን ፍቅርህን አይተካም፣ የፍልስፍናህ ጥግም ሆነ የልሂቅነትህ ጠገግ አፍቃሪነትህን አይተካከልም።

የአብሮ መኖር እንከናችንን የሚደፍን ሕብር እንጂ የመለያየት ግንብ የሚገነባ መዝሙር ሰልችቶናል፣ ከነበርክበት 'የተሻለ' ብርሃን ስትፈልግ ወደ አልነበርክበት ጨለማ አለመግባትህን ማረጋገጥ ብልህነት ነው!!

  ደምስ ሰይፉ

ውብ ጊዜ

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanityBot