Get Mystery Box with random crypto!

የተሻለ አለህ በአውሎ ንፋስ ውስጥ ብትሆን፣ ዶፍ ዝናብ ቢወርድብህ፣ ዋጋህ ያነሰበት፣ መኖርህ የማ | ስብዕናችን #Humanity

የተሻለ አለህ

በአውሎ ንፋስ ውስጥ ብትሆን፣ ዶፍ ዝናብ ቢወርድብህ፣ ዋጋህ ያነሰበት፣ መኖርህ የማይቆጠርበት፣ አበርክቶትህ የማይታይበት፣ ስራህ የማያፈራበት፣ ማንነትህ የማይመረጥበት ስፍራ ብትኖር እንኳን ፈጣሪ አብሮህ ካለ ሁሌም የተሻለ ከፍ ያለ ነገር አለህ።

ምንም እንኳን እምነታችን ቢጎድል፣ ክፋታችን ቢበዛ፣ ሃሳባችን ቢያንስ፣ ምግባራችን የወረደ፣ ስራችንም አሳዛኝ ቢሆንም ፈጣሪ ግን ጥሎ አይጥለንም።፣ ትቶ አይተወንም ሁሌም ይመለከተናልና መቼም ችላ አይለንም። የተውን ሰዎች ይኖራሉ፣ ያገለሉን፣ የተጠየፉን እንዲሁ እንደዋዛም የናቁን ሰዎች ይኖራሉ ዋናው ነገር ግን በፈጠረን አለመገፋታችን አለመረሳታችን ነው።

የተሻለ አለህ! ከዛሬው የላቀ፣ ከትናንት የገዘፈ፣ ከአሁንህ ያየለና ከፍ ያለ ስፍራ ይኖርሃል። የማይቀየሩ የሚመስሉ ከባድ ሁኔታዎች ይቀየራሉ፤ ይወርዱ የማይመስሉ ሸክሞች፣ ይፈቱ ያልመሰሉ ችግሮች፣ ይስተካከሉ ያልመሰሉ ውጥንቅጦች ይወርዳሉ፣ ይፈታሉ፣ ይስተካከሉ።

እምነትህ ቢፈተን ግራ አትጋባ ይልቅ ለተሻለ ክብር እንደታጨህ አስተውል፤ በፈተናህ ብዛት አትደናገር ይልቅ የድልህ ቀን ቅርብ እንደሆነ አስተውል። በጫናዎች ብዛት የማትሸበር፣ ለምድራዊ ፈተና የማትበገር፣ ከፈጣሪህ ውጪ እንዳልሆንክ አስተውል።

አንዳንዴ ማሳለፍ እየቻልን አቅፈናቸው የምንቀጥላቸው ብዙ ኮተቶቻችን ጣእሙን ማየት እንዳንችል ሁሉ ነገራችንን ዘግተንባቸዋል። ለማማረር እንጂ ለማመስገን ስንፈናል ለማዘን እንጂ ለመደሰት ጉልበት አጠተናል። መቆየት በማይገባን ቦታ ላይ በመቆማችን ማሳለፍ የሚገባንን አላፊ ሃሳቦችን እንዳያልፋ መንገድ ዘግተንባቸዋል እሰኪ ነቅነቅ እንበል እናሳልፋቸው የሚመጡት ሁሉ እንደአመጣጣቸው እንሸኛቸው አኛም ከቆምንበት አስተሳሰብ ስናልፍ ሁሉም ጊዜያዊ መሆኑን እናውቃለን።

ሁሉም ያልፍ የለ ትላንትናም አልፏል ዘሬም ታልፋለች ነገም ትቀጥላለች እኔም አንተም እናልፋለን ምክንያቱም ሁሉም ያልፋል።ሁሉን የፈጠረ፣ ሁሉን የያዘ፣ በሁሉ ውስጥ ያለው አምላክህ ባንተ ውስጥ ስለመኖሩ አትጠራጠር፤ ለተሻለው ስፍራ እንደሚያበቃህ እምነት ይኑርህ።

ማሰብ ላይ በርታ፤ መስራት ላይ ጠንክር፣ አምላክህን ይዘህ ፈተናህን ተጋፈጥ፣ በፀሎትህ ፅና፣ ምስጋናህን ደጋግመህ አቅርብ፣ ካንተ በላይ የሚሰራብህ፣ ተአምር የሚያደርግብህ ፈጣሪህ አብሮህ እንደሆነ አስብ። ብቻህን የሆንክ ቢመስልህ እርሱ ከጎንህ አለ፤ የተገፋህ ቢመስልህ በእርሱ እቅፍ ውስጥ ነህ፤ የወደክ ቢመስልህ እርሱ ያነሳሃል፤ በሚገባህ ስፍራም በክብር ያቆምሃል።

ውብ አሁን

@EthioHumanity
@EthioHumanity

@EthioHumanitybot