Get Mystery Box with random crypto!

ወዳጄ ሆይ ሥር የሰደዱ ዛፎች ነፋስን ይቋቋማሉ ፣ ወደ ታች የጠለቁ መሠረቶች ብዙ ፎቅ ይሸከማሉ | ስብዕናችን #Humanity

ወዳጄ ሆይ

ሥር የሰደዱ ዛፎች ነፋስን ይቋቋማሉ ፣ ወደ ታች የጠለቁ መሠረቶች ብዙ ፎቅ ይሸከማሉ ። ሰውም በሳል ሲሆን በፈተና ይጸናል ፣ ፈተናና ነፋስ ያልፋሉና ። ነፋሱ ዘንበል ቢያደርግህም እንዲሰብርህ መፍቀድ የለብህም ። ብዙ ጫናዎችን ለመሸከም እውቀትና ማስተዋልን ገንዘብ አድርግ ። አንተም እንደዛፉ ስር ስደድ ጠንካራነት እውቀት አለው ፣ በጥበብ ይናገራል ፤ ተግባር አለው ። ጠንካራነት ስሜት ሳይሆን ተግባር ፣ ፉከራ ሳይሆን ድርጊት ነው ። ጠንካራነት ሞራልም ምግባርም ነው።

ወዳጄ ሆይ

ፊት የልብ አደባባይነውና ሁሉን ቅሬታህን ፊትህ ላይ አታስነብብ፡፡ ጠላቶችህ ፊትህን እንጂ ልብህን እንዲያዩ አትፍቀድ፡፡ ለስድባቸው ስድብን አትመልስ ጆሮ ሰጥቼ ሰምቻችኀለሁ ማለት ነውና፡፡ ለአሳማሚዎችህ በቸኛው ማለፊያ ታምሞ አለመጠበቅ ነው ። ታመህ ካልጠበቀቻው ጆሮ ሰትጠህ ዝቅ ካላልክላቸው የሚያሳምምህ የለምና፡፡ ከራስህ ጋር ሳትመክር ከሰው ጋር አትመካከር፡፡ ለአንድ ሀሳብ የሶስት ቀን እድሜ ስጠው፡፡ ባዕድ ባለበት ስለቤትህ አታውራ፡፡  ለግቢህ አጥር ፣ለቤትህ በር፣ለህይወትህ ሚስጥር ይኑርህ፡፡ የተሻልክ ሳይሆን የበለጥክ ሁን፡፡

ወዳጄ ሆይ

መሬትህ በሚሸከመው መጠን ቤትህን ሥራ ፣ ወዳጅህ በሚችለው መጠን ምሥጢር ንገረው ፣ ተማሪህ ባደገበት መጠን መግበው ። የሌላው የሆነችውን ሴት ላንተ አትመኝ ። ያንን ጥላ ስትመጣ አንተን ጥላህ መሄድ እንደምትችል እያስተማርካት ነው ። አንቺም የሌላውን ባለትዳር አትመኚ ።

ወዳጄ ሆይ

ብትታመም በአገርህ ትታመማለህ ። አገርህ የታመመች ከሆነች ግን ዓለም ዝግ ይሆንብሃል ። ተሰደህም ለመከበር አገር ያስፈልግሃል ። ከሰላም የበለጠ ሀብት ፣ ከማስተዋል የበለጠ ሥልጣኔ ፣ ከፍቅር የበለጠ ደስታ የለም ። ያለ ፈጣሪ እየተስፋፉ ያሉ ሰዎች እየጠበቡ ነው ። ልብስ ጸድቶ ልብ ከቆሸሸ የመንፈስ ነጻነት ገና አልመጣም ። የድሮ ሰው ልቡ ንጹሕ ፣ ልብሱ አዳፋ ነበር ። የዛሬ ልጅ ልብሱ ንጹሕ ፣ ልቡ ሸርታታ ነው።

ወዳጄ ሆይ

የሰብዊነት ሥራ ለሰው ሁሉ የሚደረግ የደግነት ስራ ነው፣ ደግ ለመሆን ጥግ አትያዝ ። ከሥርህ ያለው አንተ የማትችለውን የሚችልልህ ነውና አክብረው ። ቆጥረህ ከሰጠህ ስጦታህ ይረክሳል ። ደብቀህ ከሰጠህ ስጦታህ ሲወራ ይኖራል ። ከፍ ስትል ልታይ ካልክ ሁሉም ሰው ስትወድቅ ያይሃል ። በከፈትክለት መጠን ጠላት ይገባል ። ሰይጣን አስገድዶ ሳይሆን አዘናግቶ የሚገድል ጠላት ነው ።

እናም ወዳጄ

የታወከ ሌሊት ሲገጥምህ በሰላም ስላደርክባቸው ሌሊቶች አለማመስገንህን አስብ ። ቀኑ መብትህ ሳይሆን ስጦታህ ነውና አመስግንበት ። እሰይ ነጋ ማለት ሲገባህ ደሞ ነጋ አትበል ።ሲያነጋልህ ምንም ክፈያ ላላስከፈለህ ጌታ የማለዳ ምስጋና ለማቅረብ አትዘግይ ። ወጥቶ የመግባት ዋጋው ትልቅ ነውና የምሽት ጸሎትህንም አታስታጉል ። እያጣጣርክ ስለ ጤና ከመጸለይ በጤናህ ፈጣሪህን አመስግን ።

ውብ ጊዜ

@Ethiohumanity
@Ethiohumanity

@EthiohumanityBot