Get Mystery Box with random crypto!

የኢትዮጵያ መንግስት የዴር ሱልጣን ገዳም ይዞታን ማስጠበቅ እንዳለበት እስራኤል አስታወቀች፡፡ በግ | Ethio Fm 107.8

የኢትዮጵያ መንግስት የዴር ሱልጣን ገዳም ይዞታን ማስጠበቅ እንዳለበት እስራኤል አስታወቀች፡፡

በግብፅ ኮፕቲክና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መካከል አለመግባባት የሚፈጥረው የዴር ሱልጣን ገዳም ይዞታ፣ የኢትዮጵያ ሆኖ እንዲዘልቅ እንደሚፈልግም የእስራኤል መንግስት ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግሯል፡፡

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለሊ አድማሱ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር ባደረጉት ቆይታ፤የኢትዮጵያ መንግስት እየሩሳሌም የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያን ንብረት የሆነውን የዴር ሱልጣን ገዳም ይዞታ ማስጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡

የእስራኤል መንግስት የዴር ሱልጣን ገዳም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ይዞታ ነዉ ብሎ እንደሚያምንም አምባሳደሩ ነገረዉናል፡፡
ነገር ግን ጉዳዩ የፖለቲካ ጥቅም ግጭት ያለበት በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመሆን ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት እንዳለበት አምባሳደሩ አስታዉቀዋል፡፡

በቅድስቲቱ ሀገር በኢየሩሳሌም ክርስቶስ የተሰቀለበት፤ የተቀበረበት፤ እንዲሁም በተነሳበት ስፍራ በጎልጎታ ተራራ ላይ ይገኛል የዴር ሱልጣን ገዳም፡፡
ከ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በገዳምነት ይጠቀሙበትና ይኖሩበት እንደነበር የሚነገርለት በሀገረ እስራኤል በኢየሩሳሌም የሚገኘው የዴር ሡልጣን ገዳም፣ በተለያየ ጊዜ የባለቤትነት ጥያቄ ይነሳበታል፡፡
በተለይ የግብፅ ኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን የባለቤትነት ጥያቄ ስታነሳ ቆይታለች፡፡ በተደጋጋሚም ገዳሙ ዉዝግብና ግጭቶችን ያስተናግዳል፡፡


ይዞታዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እንደሆነ ቢነገርም፣ ግብጻዉያኑም የይገባኛል ጥያቄ በማንሳት ለዘመናት ዉጥረትን የሚያስተናግድ የእምነት ቦታ ነዉ፡፡
የኢትዮጵያ ንግሥት ሳባ ኢየሩሳሌም በሄደችበት ጊዜ እስዋን የተከተሉ ሰዎች ያረፉበት ነበር በሚባለዉ በዚሁ በቅዱሱ ስፍራ ጎልጎታ የሚገኘዉ በዴር ሱልጣን ገዳም፣ ስያሜዉ በጥንት ዘመን በአረቦች የተሰየመና የንጉሥ ገዳም የሚል ትርጉም እንዳለዉ ስለገዳሙ የሚያዉቁ ይናገራሉ።

ለመሆኑ ግብፆች በምን አግባብ ገዳሙ የእኛ ነዉ ሊሉ ቻሉ? ስንል በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለሊ አድማሱን ጠይቀናል፡፡
አምባሳደሩ ሲመልሱ “ቀደም ባለዉ ጊዜ የኢትዮጵ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ያን አባቶች በገዳሙ ዉስጥ እንዲጠለሉ አንድ የግብጽ መነኩሴ በማስጠጋታቸዉ ግብጾቹ የእኛነዉ የሚል እሳቤ እንዳደረባቸዉ” ነግረዉናል፡፡

በዴር-ሱልጣን ገዳም የግሪክ ኦርቶዶክሶ ቤተክርስትያን፤ የሮማን ካቶሊካዉያን ቤተክርስትያን፤ የሶርያ ኦርቶዶክሶ ቤተክርስትያን፤ የአርመን ኦርቶዶክሶ ቤተክርስትያን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እና የግብጽ ኮፕት ቤተክርስትያን ይገኙበታል።

በአባቱ መረቀ

ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም

ለታማኝና ወቅታዊ መረጃዎች ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።
Telegram https://t.me/ethiofm107dot8
YouTube https://www.youtube.com/.../UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/videos