Get Mystery Box with random crypto!

“በደመወዝ ጥያቄ ሽፋን፣ ሁከት እና ብጥብጥ አስነስታችኋል” በሚል ለእስር የተዳረጉት 40 ሰራተኞች | Ethio Fm 107.8

“በደመወዝ ጥያቄ ሽፋን፣ ሁከት እና ብጥብጥ አስነስታችኋል” በሚል ለእስር የተዳረጉት 40 ሰራተኞች እያንዳንዳቸዉ በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተለቀቁ፡፡

በደቡብ ክልል ሀዲያ ዞን ምስራቅ ባድዋቾ ወረዳ ለወራት ያልተከፈላቸውን ደመወዝ ይከፈለን በሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ታስረው የነበሩት ሰራተኞች ከእስር መፈታታቸውን ኤትዩ ኤፍ ኤም አረጋግጧል፡፡
ከ40 በላይ ቀናት በእስር መቆየታቸውን የተናገሩት እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት ግለሰቦቹ አሁን በዋስትና ተፈተው ከቤተሰብ መቀላቀላቸውን ለጣቢያችን ገልጸዋል፡፡

ከሚመለከተው አካል ጋር ንግግር እያደረጉ መሆኑን የሚናገሩት ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት ያናገርናቸው ግለሰብ “በህግ ቁጥጥር ስር ስውል በተፈጸመብኝ ድብደባ ህክምና ማግኘት ባለመቻሌ በአንድ አይኔ ላይ ከፍተኛ የጤና ችግር ድርሷል” ብለዋል፡፡
ከተፈጸመባቸው የመብት ጥሰት በተጨማሪ፣ ሕክምና መከልከላቸውንም ተናግረዋል፡፡

ከእስር የተፈቱት ችግሩ ተፈቶ እንደሆነ የጠየቅናቸው ግለሰቦቹ " አይ በፍጹም፤ ዐቃቤ ሕግ በማስረጃ የተደገፈ ክስ ማቅረብ ባለመቻሉ ነፃ ናችሁ በሚል ነው እያንዳንዳችን በ50ሺህ ብር ዋስ የተፈታነው ” ብለዋል፡፡

በእስር ላይ ከነበሩት መካከል ሌላኛው ስሜ አይጠቀስ ያሉን ግለሰብ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቁይታ እንደነገሩን፤ በውድቅት ሌሊት በር ሰብረው በገቡ የጸጥታ ሀይሎች እሳቸው እና ሌሉች አምስት የቤተሰቡ አባላትን ስብእናን በሚነካ መልኩ መወሰዳቸውን ገልጸው ከባድ የተባለ ድብደባም ተፈጽሞብናል ነው ያሉት፡፡
“በደመወዝ ጥያቄ ሽፋን ሁከት እና ብጥብጥ አስነስታችኋል ፤ለመገናኛ ብዙሀን እና በማህበራዊ ሚዲያም ዞናችን ስም አጥፍታችኃል በሚልም ክስ ቀርቦብን ነበር ኋላ ግን በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተለቀናል” ብለውናል፡፡

“አሁንም ድረስ የሾኔ ሆስፒታል ደሞዝ ለሰራተኞቹ መክፈል ባለመቻሉ ስራ እንዳቆመ ተናግረው ሌሎች ወረዳዎች ላይም ችግሩ ተባብሶ ቀጠለ እንጂ መፍትሔ አልተሰጠንም” ብለውናል ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት ግለሰቦች፡፡

የሃዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ሜጫ ስለጉዳዩ ምላሽ እንዲሰጡን ተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስልክ ሊያነሱልን አልቻሉም፡፡

ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ከአንድ የውጪ የዜና ወኪል ጋር በነበራቸው ቁይታ፤ ታስረው የነበሩ ሠራተኞች የዋስትና መብታቸው ተፈቅዶ መለቀቃቸውን ገልጸው፣ “ጉዳዩ ግን ገና አልተቋጨም ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በያይኔአበባ ሻምበል

ሰኔ 01 ቀን ቀን 2015 ዓ.ም

ለታማኝና ወቅታዊ መረጃዎች ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።
Telegram https://t.me/ethiofm107dot8
YouTube https://www.youtube.com/.../UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/videos