Get Mystery Box with random crypto!

ግብጽ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግደቡ ዙሪያ አሳሪዉን ስምምነት እንድትቀበል ጠየቀች፡፡ የግብጹ ፕሬዝዳን | Ethio Fm 107.8

ግብጽ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግደቡ ዙሪያ አሳሪዉን ስምምነት እንድትቀበል ጠየቀች፡፡

የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ አሳሪዉን ስምምነት እንድትቀበል አሳስበዋል፡፡

አልሲሲ ከሞሪታኒያዉ አቻቸዉ ጋር ባደረጉት ዉይይት ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ መፍትሄ ለማምጣት ልትስማማ ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በዉይይታቸዉም የግብጽን የዉሃ ደህንነት ማስጠበቅ ለአረቡ ዓለም ጸጥታ እና ደህንነት ዋስትና መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ መግባባት ላይ እንዲደረስም ፕሬዝዳንቱ ጠይቀዋል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት በማሳየት የታችኛዉን ተፋሰስ አገራት ጥቅም እንዲጠበቅም አልሲሲ ጠይቀዋል፡፡

የአሁኑ የግብጽ ማሳሰቢያ ኢትዮጵያ አሳሪዉን ስምምነት እንድትፈርም እንዲሁም በግድቡ ሙሌትና አስተዳደር ላይ የጋራ መግባባት እንዲኖር መሆኑን ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል፡፡

በቅርቡ ግብጽ በአረብ ሊግ ጉባዔ ላይ በግድቡ ጉዳይ ላይ የአረብ አገራት እጃቸዉን እንዲያስገቡ መጠየቋ ይታወሳል፡፡

ግብጽ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሶስቱ አገራት አልፎ የአረብ የደህንነት ስጋት ነዉ በሚልም ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ትከሳለች፡፡

ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በግድቡ ዙሪያ የአረብ ሊግ ያወጣዉን መግለጫ ዉድቅ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በግድቡ ዙሪያ ሲያካሂዱት የነበረዉን ድርድር ካይሮ ፣ አዲስ አበባ አሳሪዉን ስምምነት ካልፈረመች አሻፈረኝ በማለቷ ዉይይቱ መቋረጡም ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ግን በግድቡ ዙሪያ ያሉትን አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልጻል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አራተኛዉ ዙር የዉሃ ሙሌት በቀጣይ የክረምት ወቅት እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡

በእስከዳር ግርማ
ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም

ለታማኝና ወቅታዊ መረጃዎች ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

YouTube https://www.youtube.com/.../UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/videos