Get Mystery Box with random crypto!

በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ድርጊት በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል---ኢሰመኮ | Ethio Fm 107.8

በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ድርጊት በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል---ኢሰመኮ
////

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች እየጨመረ የመጣውን የአስገድዶ መሰወር (Enforced Disappearance) እና ተይዘው የሚገኙበት ሁኔታ ሳይታወቅ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ጉዳይ ሲከታተል መቆየቱን ለኢትዮ ኤፍ ኤም በላከው መግለጫ አሳውቋል።

በተለይም ይህ አሳሳቢ ሁኔታ በተከሰተባቸው የአዲስ አበባ ከተማ፣ የኦሮሚያ ክልል እና የአማራ ክልል ኮሚሽኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን መንግሥታዊ ኃላፊዎች በማነጋገር፣ በልዩ ልዩ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ቦታዎች በመዘዋወር እና ከቤተሰቦችና ከሌሎች የመረጃ ምንጮች መረጃዎችን ሲያሰባስብ እንደቆዬ አመልክቷል።

ኢትዮጵያ ገና ያላጸደቀችው ቢሆንም ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ በተደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት (International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance) መሠረት አስገድዶ መሰወር ማለት “በመንግሥት ወኪሎች ወይም ከመንግሥት ፈቃድ ወይም ድጋፍ በተሰጣቸው ሰዎች ወይም ቡድኖች ወይም በመንግሥት ስምምነት አንድን ሰው በማሰር፣ አፍኖ በመውሰድ፣ ወይም በሌላ በማናቸውም መንገድ ነጻነቱን በማጥፋትና፤ በቁጥጥር ስር መዋሉን በመካድ፣ በመደበቅ፣ የአለበትን ቦታ ባለማሳወቅ ወይም ደብዛውን በማጥፋት ፈጽሞ ከሕግ ጥበቃ ውጪ እንዲሆን ማድረግ’’ ነው።

በሌላ በኩል አንድን ሰው የሚገኝበት ቦታና ሁኔታ ሳይታወቅ በእስር መያዝ ማለት በተለይ በከባድ ወንጀል ተጠርጥሯል የተባለን ሰው ለወንጀል ምርመራ በሚል ምክንያት ከቤተሰብ እና ከጠበቃ እንዳይገናኝ አድርጎ በእስር የማቆየትን ተግባር የሚገልጽ ፅንሰ ሐሳብ ሲሆን፤ እነዚህ ሁለቱም ድርጊቶች ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ናቸው።

በተለይ በአስከፊነቱ የሚታወቀው የአስገድዶ መሰወር ተግባርን የሚያቋቁሙት ዋነኛ አላባዎች ሦስት ዋና ጉዳዮች ናቸው ያለው ኮሚሽኑ፣በማናቸውም ዓይነት መንገድ ቢሆን አንድን ሰው ከፈቃዱ ውጪ ነጻነቱን መንፈግ/ማጥፋት፣ መንግሥት በጉዳዩ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ፈቃድ ወይም ድጋፍ ወይም ስምምነት በመስጠት ተሳታፊ መሆን እና
አስገድዶ የተሰወረውን ሰው ያለበትን ቦታ እና ሁኔታ መካድ፣ አለመቀበል ወይም ለማሳወቅ ፈቃደኛ አለመሆን መሆናቸውን አብራርቷል፡፡

ኢሰመኮ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከደረሱት አቤቱታዎችና ጥቆማዎች በመነሳት ሲያደርግ በነበረው ክትትል መሠረት በርካታ የአስገድዶ መሰወርን ድርጊት የሚያቋቁሙ ድርጊቶች መከሰታቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

አብዛኛውን ጊዜ የዚህ ድርጊት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሥራ ቦታ ወይም ከመንገድ ላይ የሲቪልና የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ጸጥታና ደኅንነት ሠራተኞች ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ ተይዘው ከታሰሩ በኋላ ወዳልታወቀ ስፍራ እየተወሰዱ እንዲሰወሩ የተደረጉ ሲሆን፤ ከፊሎቹ ከተወሰኑ ቀናት፣ ሳምንታት ወይም ወራት መሰወር በኃላ የተገኙ መሆናቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ ሌሎች ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ በግዳጅ እንደተሰወሩ የቀጠሉ ናቸው።

ከእነዚህ ተጎጂዎች መካከል የተወሰኑት ሲያዙ በወንጀል ተጠርጥረው የሚፈለጉ መሆኑ ተነግሯቸው ወደ መደበኛ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኋላ የተሰወሩ ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ ምንም ሳይነገራቸው በጸጥታ ኃይሎች ተወስደው የተሰወሩ ናቸው ብሏል፡፡

ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚያዝያ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ ብቻ በማስገደድ ተሰውረው ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ከተለያየ የጊዜ መጠን መሰወር በኃላ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው የተገኙ ሲኖሩ፣ አስገድደው በተሰወሩበት ወቅት በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ውስጥ ገላን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ የቀድሞው ልዩ ኃይል ካምፕ ውስጥ ተይዘው እንደቆዩ ለመረዳት ተችሏል። በአስገድዶ መሰወሩ ወቅት ተፈጽሟል ስለተባለ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ ወይም የማሰቃየት ተግባር ኮሚሽኑ ምርመራውን የቀጠለ ሲሆን የምርመራ ሥራው እንደተጠናቀቀ ትክክለኛውን መረጃ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ይህ አስከፊ የሆነ የአስገድዶ መሰወር ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም መንግሥት አስፈላጊውን ጊዜያዊ እና ዘለቄታዊ እርምጃዎች ሁሉ እንዲወስድ፣ የተሰወሩ ሰዎች ሁሉ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ፣ በተሰወሩበት ጊዜ ሁሉ የተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ የተሟላ ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ችግሩ የደረሰበትን አሳሳቢ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ሀገር አቀፍ ገለልተኛ አጣሪ የሥራ ቡድን በማዋቀር የድርጊቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ማፈላለግ እና ፍትሕን ማረጋገጥ ይገባል” በማለት አሳስበዋል።

ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም

ለታማኝና ወቅታዊ መረጃዎች ከታች ያሉትን ገፆቻንን ይጎብኙ ቤተሰብ ይሁኑ ።

Telegram https://t.me/ethiofm107dot8

YouTube https://www.youtube.com/.../UCn4D20GPsAtNqN5bIC1BhFA/videos