Get Mystery Box with random crypto!

የግንባታ ሥራ  ውል አፈጻጸም ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ ዋና ዋና  ባለድርሻ አካላት፡ የስራው ባለቤት | Ethio Construction

የግንባታ ሥራ  ውል አፈጻጸም ውስጥ ተሳታፊ የሚሆኑ ዋና ዋና  ባለድርሻ አካላት፡

የስራው ባለቤት/Client/Employer:-

ግለሰብ ወይም ማህበር ወይም ድርጅት ወይም የመንግስት ተቋም ሊሆን የሚችል ሲሆን የሥራው ባለቤት ከመሆኑ አንጻር ሥራውን ለማከናወን የሚችል ሥራ ተቋራጭና አማካሪ መሃንዲስ መቅጠር እና ለግንባታ ሥራው የሚያስፈልገውን የገንዘብ ሀብት የሚያዘጋጅና ዋጋ የመክፈል ሃላፊነት ያለበት አካል ነው፡፡

ሥራ ተቋራጭ:-

ይህ ባለድርሻ አካል ከባለቤት ጋር በፈጸመው ውል ስምምነት መሰረት ለሥራው አስፈላጊ የሆኑትን ግብዓቶች በሙሉ በሟሟላት የግንባታ ሥራውን  በተባለው ጊዜና በተቀመጠው የጥራት ደረጃ ለመስራት ተዋውሎ የሚሰራ ነው፡፡

መሃንዲስ(አማካሪ):-

ይህ ባለድርሻ አካል ከባለቤት ጋር በፈጸመው ውል ስምምነት መሰረት ውለታውን እንዲያስተዳድር የሚቀጠር ነው፡፡ምንም እንኳን አማካሪ መሃንዲሱን የሚቀጥረውና ክፍያ የሚፈጸምለት በአሰሪው ቢሆንም፤ አማካሪው ውሉን በማስተዳደር ሂደት ውስጥ በቅን ልቡና በፍጹም ፍትሃዊነት ለሁለቱም የሚሰራ ነው፡፡

የመድን ዋስትና ሰጪ ድርጅቶች (Insurance Companies):-

አንድ ሥራ ተቋራጭ በጨረታ ለመሳተፍ፣ ወደውል ለመግባት፣ ክፍያዎች ለማግኘትና በሌሎች አሰሪው ድርጅት ለደህንነቱ መጠበቂያ ከስራ ተቋራጩ እንዲቀርብለት የሚጠይቀውን የመተማመኛ የመድን ዋስትናዎች ለሥራ ተቋራጩ የሚያቀርብ አካል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሥራ ተቋራጩ በአጠቃላይ ለንብረቱ፣ ለገንዘቡ፣ ለስራውና ለሰራተኞቹ ደህንነት የሚጠይቃቸውን የመድን ዋስትናዎችንም (for Contractor’s all risks) የሚያቀርብ ይሆናል፡፡ አንድ የመድን ዋስትና ሰጪ ድርጅት አይነቱ ተለይቶ ለታወቀ ጉዳይ ለሥራ ተቋራጩ የመድን ሽፋን ሰጠ ማለት በአሰሪው ድርጅትና በሥራ ተቋራጩ በኩል ሊኖር የሚችለውን የአደጋ ስጋት ለመሸከም ሃላፊነት የሚቀበል ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለወደፊት ስለግንባታ ፕሮጀክቶች የመድን ዋስትናዎች (Construction Insurances) በተብራራ ሁኔታ በምናቀርበው ጽሁፍ የምናየው ይሆናል፡፡

ባንኮች:-

ለስራ ተቋራጩም ይሁን ለስራው ባለቤት ለፕሮጀክቱ ማከናወኛ የገንዘብ ፍላጎቶችን በማመቻቸት የሚሰሩ ናቸው፡፡ ባንኮች እንደ የጨረታ ማስከበሪያና የውል ማስከበሪያ የባንክ ዋስትናም በመስጠት የሚሰሩ ናቸው፡፡ 

አቅራቢዎች (Suppliers):-

እነዚህ ባለድርሻ አካላት ለግንባታ ሥራ ከመጀመሪያ እስከ ሥራው ፍጻሜ የሚያስፈልጉ ማናቸውንም ዓይነት የግንባታ ሥራ ግብዓቶችን፣ ማሽነሪዎችን ወይም የግንባታ ሥራ ቁሳቁሶችን በሽያጭና በኪራይ  የሚያቀርቡ ናቸው፡፡

ፈቃድ ሰጪ አካላት (Permitting bodies):-

ለግንባታ ሥራው የግንባታ ቦታ በመፍቀድ፣ የግንባታ ፈቃድ በመስጠት፣ የግብዓት ማውጫ ካባዎችን ፣የማምረቻ የማከማቻና የቆሻሻ ማስወገጃ ቦታ ፈቃድ በመስጠት የሚሰሩ ናቸው፡፡

የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅራቢ ተቋማት (Public):-

ለግንባታ ሥራው እንደ ውሃ፣መብራት፣ስልክ የመሳሰሉ ለግንባታ ሥራዎች የመሰረታዊ አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ አካላት ናቸው፡፡


https://t.me/ethioengineers1