Get Mystery Box with random crypto!

ተቋራጭን ከሳይት ስለማባረር/Expel right/ በዚህ ጽሁፍ ተቋራጭን ከግንባታ ስፍራ/ሳይት | Ethio Construction

ተቋራጭን ከሳይት ስለማባረር/Expel right/

በዚህ ጽሁፍ ተቋራጭን ከግንባታ ስፍራ/ሳይት የማባረር መብት ለማን የተሰጠ ነው?በየትኛው ህግ?በምን ሁኔታ?በየትኛው የውል አይነት?በዚህ ጊዜ ማን ምን መስራት አለበት?የሚሉትን በአጭሩ ለመጠቆም እንሞክራለን፡፡
#ይህ መብት ያለው የትኛው አካል ነው? የሚለውን በተመለከተ ተቋራጭን ከግንባታ ሳይት/ከግንባታ ስፍራ ለማባረር መብት ያለው አሰሪው ነው፡፡ስለዚህ መብቱ የግንባታው ባለቤት ወይም የአሰሪው ነው፡፡ስለዚህ ይህን መብት ተቋራጮች ሆኑ አሰሪ ያልሆነ ሌላ አካል ተግባራዊ ሊያደርገው አይችልም ማለት ነው፡፡
#በየትኛው ህግ? ለሚለው ምላሹ በፍትሀብሄር ህጉ እና በጀኔራል ኮንዲሽነን ኦፍ ኮንትራክት ነው፡፡በዝርዝር ሲታይ፡-
-በግንባታ ውሎች በተለይ ጀኔራል ኮንዲሽነን ኦፍ ኮንትራክት መጠቀም የተለመደ ነው፡፡እነዚህ ጀኔራል ኮንዲሽኖች በራሳቸው ህግ አይደሉም፡፡እዚህ ላይ አንዳንድ የህግ ባለሙያዎች እንደ መመሪያ እና ህግ ስለሚቆጥሩት ይህ የግንዛቤ ክፍተት መታረም ይኖርበታል፡፡የግንባታ ውል ተዋዋዮች በስምምነታቸው እነዚህን ጀኔራል ኮንዲሽኖች የውሉ አካል ሲያደርጓቸው በፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 1731 መሰረት በተዋዋዮች መካከል እንደ ህግ ሆነው ይቆጠራሉ፡፡እዚህ ላይ ሌላው ጉዳይ ስፔሻል ኮንዲሽን ኦፍ ኮንትራክት ተብለው የሚቀመጡት ከጀኔራል ኮንዲሽኑ ድንጋጌዎች የተፈጻሚነት ቅድሚያ ይኖራቸዋል፡፡ለምሳሌ ከነዚህ ጀኔራል ኮንዲሽኖች ውስጥ የሲቪል ግንባታ ስራዎች ቋሚ የውል መተዳደሪያ/Standard condition of contract for the construction of civil work projects/ አንዱ ነው፡፡ይህ ጀኔራል ኮንዲሽን በከተማ ልማት ሚኒስቴር በኩል የተዘጋጀ ሲሆን ይዘቱ በዋናነት ከFIDIC 1987 version የተወሰደ ነው፡፡በአብዛኛው MoWUD 1994 ተብሎ ይጠራል፡፡ሆኖም ዋናው ነጥብ ተዋዋዮች ጥቅም ላይ ያዋሉትና የውላቸው አካል ያደረጉት የትኛውን ጀኔራል ኮንዲሽን እንደሆነ መለየትና ማወቅ የግድ ይላል፡፡
-ከዚህ አንጻር MoWUD 1994 ክሎዝ 63 ተቋራጭን ከግንባታ ስፍራ/ሳይት የማባረር መብትን አስመልክቶ በዝርዝር አስቀምጦታል፡፡በዚህ ድንጋጌ መሰረት በዋናነት አማካሪ መሀንዲሱ ለአሰሪው የተቋራጩን እንደውሉ ያለመፈጸም ሲያሳውቅ በተለይም ተቋራጩ ስራውን እንደተወው አማካሪው ሲያስታውቅ፣ተቋራጩ በአማካሪ መሀንዲሱ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው ለ28ቀናት ስራውን ሳይጀምር ሲቀር፣በመሀንዲሱ ተቀባይነት የላቸውም የተባሉ የግንባታ ቁሳቁሶችን በ28 ቀናት ውስጥ ከሳይት ያላስወጣ እንደሆነ፣በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ እየተሰጠው ስራውን በውሉ አግባብ ለመፈጸም ፈቃደኛ ያልሆነ እንደሆነ፣አማካሪ መሀንዲሱ እየከለከለው የስራውን ክፍል ለሌላ ተቋራጭ አሳልፎ የሰጠ እንደሆነ ወይም ተቋራጩ የከሰረ እንደሆነ አሰሪው የ14 ቀን ማስጠንቀቂያ በመስጠት ተቋራጭን ከግንባታ ስፍራ/ሳይት ማባረር የሚችል ይሆናል፡፡በዚህ ጊዜ ውሉ ይቋረጣል ማለት ነው፡፡/Termination of contract/
-በፍትሀብሄር ህግ አንቀጽ 3288 አና ተከታዮቹ ላይ የተደነገገውም ተቋራጩ የውል ግዴታውን ባልፈጸመ ጊዜ የግንባታ ባለቤት ለሆነው ለአስተዳደር መስሪያ ቤት የግንባታ ስራውን ከተቋራጩ ለመንጠቅ እና ውሉ ሳይቋረጥ ስራው በስራ መሪ ስር ሆኖ እንዲቆይ ለማድረግ መብት ይሰጠዋል፡፡እንዲሁም ውሉ ሊሰረዝ የሚችልበት ፈቃጅ የውል ቃል በግንባታ ውሉ ላይ ያለ እንደሆነ አሰሪው ቀሪውን ስራ ለሌላ ተቋራጭ በጨረታ ወይም በስምምነት በማሰራት እንዲጠናቀቅ ማድረግ ይችላል፡፡/የፍ/ህ/ቁ 3291(1) በዚህም ምክንያት አሰሪው ለተጨማሪ ወጭ/Additional cost/ የተዳረገ እንደሆነ ከተቋራጩ ላይ ለመጠየቅ እንደሚችል የፍ/ህ/ቁ 3291(2) በግልጽ መብት ይሰጠዋል፡፡ሆኖም በውል ህግ ላይ አሰሪው የተቋራጩን ግዴታ በሚያከብድ ሁኔታ ቀሪውን ስራ ማከናወን እንደሌለበት የሚያስገነዝበውን ግዴታውንም ማክበር አለበት፡፡
#በየትኛው የውል አይነት? ለሚለው በዋናነት የአስተዳደር መስሪያ ቤት የግንባታ ውሎችን በሚመለከት ሊተገበር የሚችል ነው፡፡ በግል የግንባታ ውሎች/private construction contract/ በተለይ ከፍ/ህ/ቁ 2610 እና ተከታዮቹ እንዲሁም ከፍ/ህ/ቁ 3019 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች ውስጥ ተቋራጭን ስለማባበር አስመልክቶ ግልጽ ድንጋጌ አለመኖሩ ይህ መብት ለግለሰቦች ለመተግበር አስቸጋሪ የመሆኑን ሁኔታ ታሳቢ ተደርጐ በህግ አውጭው በማወቅ/ፐርፐዝሊ/ የተተወ ይመስላል፡፡ተዋዋዮች የግንባታ ውል ሲዋዋሉ ጀኔራል ኮንዲሽን ቢጠቀሙና በዚህም ስለተቋራጭ የማባረር መብት ድንጋጌ ቢኖረውስ የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል?ይሄን እንዴት ይተገብረዋል የሚለው ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ውሉ ግን ለተዋዋዮች ህግ ስለሚሆን በተቻለ መጠን ሊተገበር ይገባዋል የሚል እሳቤ አለኝ፡፡
#በዚህ ጊዜ ማን ምን መስራት አለበት? ለሚለው በዋናነት በ MoWUD 1994 ክሎዝ 63(2) ላይ እንደተቀመጠው በግንባታ ሳይት ላይ የተገኘ ቁሳቁስ በሙሉ በዝርዝር መመዝገብና ዋጋ ወጥቶለት መጠኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡በተቋራጩ የተሰራው ስራ መጠን/level of work done/ በትክክል መታወቅና በዝርዝር መመዝገብ አለበት፡፡ተቋራጩ ያለበት እዳ/ከወሰደው የቅድሚያ ክፍያ ውስጥ ያልመለሰው ማለት ነው/ መታወቅ አለበት፡፡ለተቋራጩ የተከፈለው የስራ ክፍያ ሊታወቅ ይገባል፡፡እነዚህን የሂሳብ ሁኔታዎች አመዛዝኖ እና ዋጋ አስቀምጦ ተቋራጩ የሚከፈለው ገንዘብ ካለ እንዲከፈለው ለአሰሪው የሚመልሰው ገንዘብ ካለም እንዲመልስ ሂሳብ የማስተሳሰብና ሪፖርት የማቅረብ ሀላፊነቱ የአማካሪ መሀንዲሱ ነው፡፡በዚህ ረገድ አማካሪ መሀንዲሶች ብዙ ጊዜ እንደዚህ አይነት ሪፖርት ስለማያቀርቡ የግንባታ ክርክሮች ያልተሸከፉ ይሆኑና ለፍርድ ቤቶች ለትክክለኛ ፍትህ አሰጣጥ አስቸገሪ ሁኔታ ይፈጥራሉ፡፡
#አሰሪው ይህን መብቱን ለመጠቀም ሀይል መጠቀም የሚችልበት ግልጽ ፈቃጅ ህግ ግን የለም፡፡
#በመጨረሻም አሰሪና ተቋራጮች ለግንባታ ጥራት በመስራትና ለትክክለኛ እና እውነተኛ ነገር በመተባበር የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ እድገት እንዲያሳይ ማገዝና አለመግባባቶችን በስምምነት መፍታት ቢችሉ ጠቀሜታው ለሀገርም ለራሳቸውም ነው፡፡በአሰሪና ተቋራጭ ክርክር ብዙ ትምህርት ቤት እና የጤና ተቋም እንዲሁም ሌሎች መሰረተ ልማቶች ግንባታቸው ተቋርጦ ማህበረሰቡን ከተጠቃሚነት የሚያዘገይበት ሁኔታ ወደፊት ተቀርፎና ተቃልሎ ማየት የዘወትር ምኞታችን ነው፡፡


By: Gubaie Assefa
https://t.me/ethioengineers1