Get Mystery Box with random crypto!

በአማራ ክልል የተፈናቃዮች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ ተነገረ፡፡ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስ | HabeshaNet.

በአማራ ክልል የተፈናቃዮች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ ተነገረ፡፡

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮምሽን እንዳለው፣ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በተለይም ከኦሮሚያ እና ከቤኒሻንጉል ክልል ተፈናቅለው ወደ ክልሉ የሚመጡ ተፈናቃዮች ቁጥር በየጊዜው በእጅጉ እየጨመረ ነው፡፡

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮምሽን ኮምሽነር አቶ ዘላለም ልጅአለም ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቁት፣ በ አሁኑ ሰዓት በክልሉ 4 መቶ 95 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ተፈናቃዮች በአብዛኛው ኦሮሚያና ቤኒሻንጉልን ጨምሮ ከትግራይ እና ከደቡብ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡

አብዛኛው ተፈናቃይ ማህረሰቡ ውስጥ አብሮ ይገኛል ያሉን ኮምሽነር ዘላለም፣ በተጨማሪም ቻግኒ፤ሰሜን ወሎ፤ ደቡብ ወሎ እና ጎንደር በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደሚገኙም ነግረውናል፡፡

እነዚህን ተፈናቃዮች የሚደግፍ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ቢሆንም፣ በማንነታቸው ምክንያት ከቀያቸው ቤት ንብረታቸውን ጥለው የመጡ ዜጎች ወደ ቀደመ ቀያቸው መመለስ እንዳለባቸው ክልሉ እንደሚያምን ነው የነገሩን፡፡

በተለይም ወደ ቀደመ ቀያቸው እንዲመለሱ የማድረጉ ስራ መንግስትና በተለይም የመጡበት ክልል ከፍተኛ ሃላፊነት ሊወስድና መልክ ማሲያዝ እንዳለበትም አስታውቀዋል፡፡

በየዉልሰዉ ገዝሙ
ሚያዝያ 06 ቀን 2013 ዓ.ም