Get Mystery Box with random crypto!

ኢትዮጵያዊው የሂሳብ ሊቅ የአሜሪካን ፕሬዝደንታዊ አዋርድ ተሸላሚ ሆኑ፡፡ ለ25 አመታት በሳቫና ስ | HabeshaNet.

ኢትዮጵያዊው የሂሳብ ሊቅ የአሜሪካን ፕሬዝደንታዊ አዋርድ ተሸላሚ ሆኑ፡፡

ለ25 አመታት በሳቫና ስቴት ዩኒቨርስቲ የማቲማቲክስ ፕሮፌሰር ሆነው የሰሩት ሙላቱ ለማ የአሜሪካን ፕሬዝደንታዊ የሳይንስ፣ የማትማቲክስና የኢንጂነሪንግ የልህቀት ሽልማት ለማግኘት ተመርጠዋል፡፡

ዩኒቨርስቲ ትላንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ፕሮፌሰር ሙላቱ የተመረጡትና ሽልማቱን የተቀበሉት ከሌሎች 12 ምሁራን ጋር ነው፡፡ ሽልማቱ ለአሜሪካ የወደፊቱ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግና ማትማቲክስ እውቀት መሰረት ለጣሉ ሊቆች የሚበረከት እንደሆነ መግለጫው አስረድቷል፡፡

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝደንት ኪምበርሊ ባላርድ ዋሽንግተን ሲናገሩ ‹‹ይህ ለፕሮፌሰር ሙላቱ ለማ ትልቅ ክብር ነው፡፡ ለበርካታ አመታት የሳቫና ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን እውቀት በመመገብ ላደረጉት አስተዋፅኦና ለዚህ ታላቅ ስኬት በመብቃታቸውም እንኳን ደስ አለዎት ለማለት እፈልጋለሁ›› ብለዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሙላቱ ሳቫና ዩኒቨርስቲን እ.ኤ.አ በ1995 ከመቀላቀላቸው በፊት በኢትዮጵያ ውስጥ አዋሽ በሚባል መለስተኛ ኮሌጅ ለአምስት አመት አስተምረዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው በመግለጫው ፕሮፌሰሩ ባለፉት አመታት እውቀት የመመገብ ስራቸው እድሜያቸው ከ12 አመት እስከ 63 አመት የሆናቸውን ተማሪዎች ማስተማራቸውን አስታውቋል፡፡

የዚህ አመታዊ ሽልማት አሸናፊ በአሜሪካ ፕሬዝደንት የተፈረመበት ሰርተፍኬት የሚበረከትለት ሲሆን ከብሄራዊ ሳይንስ ፋውንዴሽን ደግሞ አስር ሺ ዶላር ይሰጠዋል፡፡ ሽልማቱ በዋሽንግተን ዲሲ ከአሜሪካ ፕሬዝደንት እጅ የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡
ፕሮፌሰር ሙላቱ ለማን ሐበሻ Net በዚህ አጋጣሚ እንኳን ደስ አለዎት ይላል።