Get Mystery Box with random crypto!

የመከላከያ ሚኒስትሩ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነታቸው ተነሱ። የኦሮሚያ ክልልን በመወከል የፌዴሬ | HabeshaNet.

የመከላከያ ሚኒስትሩ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነታቸው ተነሱ።

የኦሮሚያ ክልልን በመወከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የነበሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳ ከአባልነታቸው መነሳታቸው ተጠቁሟል።

ሰሞኑን ደግሞ ከኦሮሚያ የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው መታገዳቸው ይታወሳል።

ከአቶ ለማ በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሆነው እያገለገሉ የነበሩት ወ/ሮ ጠይባ ሐሰንና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኦሮሚያ የመሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ሚልኬሳ ሚደጋ (ዶ/ር) ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነታቸው መነሳታቸውን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ አመልክቷል።

ጨፌ ኦሮሚያ ክልሉን በመወከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ለማ፣ ወ/ሮ ጠይባና ሚልኬሳ (ዶ/ር) ከአባልነታቸው እንዲነሱ የወሰነው ከሁለት ሳምንት በፊት ባካሄደው ስብሰባ እንደሆነም ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።

ጨፌ ኦሮሚያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በተለያዩ ምክንያቶች ተጓድለዋል በሚል ምክንያት ሦስቱ አመራሮች በሌሎች እንዲተኩ ማድረጉን መረጃዎቹ አመልክተዋል

በመሆኑም ጨፌው በሦስቱ አመራሮች ምትክ አዲስ አባላትን መርጦ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስታወቀ ሲሆን፣ አቶ ለማን ተክተው የተመረጡትም በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና በጨፌ ኦሮሚያ የክልሉ መንግሥት ተጠሪ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት አቶ ፍቃዱ ተሰማ ናቸው።

በሌሎቹ ሁለት አባላት ምትክ ደግሞ የክልሉ ፓርቲ አደረጃጀት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳዳት ነሻና አቶ አብዱል ሐኪም መመረጣቸው ታውቋል። የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ለማ ሰሞኑን በተካሄደ የፓርቲ ስብሰባ ከኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው መታገዳቸውም ይፋ ሆኗል።

የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ በአዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ ለሁለት ቀናት ያካሄደውን ስብስባ ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. አጠናቆ ባወጣው መግለጫ፣ አቶ ለማን ጨምሮ ሦስቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ላልተወሰነ ጊዜ መታገዳቸውን አስታውቋል።

የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ለሁለት ቀናት የተካሄደውን ስብሰባና ውሳኔዎቹን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፣ ስብሰባው በፓርቲው ክልላዊ መዋቅር ላይ የተስተዋሉ ድክመቶች ላይ በስፋት ተወያይቶ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን የተመለከቱ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈ ገልጸዋል።

በፓርቲው የክልል መዋቅር ከፍተኛ አመራሮች ላይ ባደረገው ግምገማም በማዕከላዊ አባልነት ሲያገለግሉ የነበሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ለማ፣ ወ/ሮ ጠይባና ሚልኬሳ (ዶ/ር) ላልተወሰነ ጊዜ ከማዕከላዊ አባልነታቸው እንዲታገዱ መወሰኑን አስታውቀዋል።

አቶ ለማ መገርሳ ከማዕከላዊ አባልነታቸው እንዲታገዱ ምክንያት ከሆኑት ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ በፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባዎች ላይ በተደጋጋሚ አለመገኘታቸው መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪም የመከላከያ ሚኒስትር ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በተጣሉባቸው መንግሥታዊ ኃላፊነቶች ላይም በተደጋጋሚ አለመገኘታቸውን አቶ ፍቃዱ በምክንያትነት አንስተዋል።

Via Ethio Fm