Get Mystery Box with random crypto!

አጭር ቀሚስ አስለብሶ የመስተንግዶ ስራ ያሰራ ሆቴል እና መሰል ተቋም እስከ 50 ሺህ ብር የሚደርስ | ኢትዮ መረጃ - NEWS

አጭር ቀሚስ አስለብሶ የመስተንግዶ ስራ ያሰራ ሆቴል እና መሰል ተቋም እስከ 50 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣው የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የቱሪስት አገልግሎት ተቋማት ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ ዳይሬክተር ወ/ሮ ገነት ይመር ለብስራት ሬድዮና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት ቢሮዉ በአዋጅ ቁጥር 74/2014 አንቀፅ 22 ቁጥር 6-13 በተሰጠዉ ስልጣን መሰረት በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዙሪያ ኢትዮጵያዊ ባህልና እሴት እየተሸረሸረ በመሆኑ የደንብ ረቂቅ አውጥቷል።

በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የገፅታና የውበት አጠባበቅ እንዲሁም የጌጣጌጥ አጠቃቀም ስነ-ስርዓት ላይ ቢሮዉ ያወጣዉን የደንብ ረቂቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ጉዳዩን የጋራ አድርጓል።በረቂቅ ደንቡ መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ በሆቴሎችና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች የሚለብሷቸው ልብሶች እና የሚያደርጓቸው ጌጣጌጦች የኢትዮጵያን ባህል እና እሴት የጠበቁ መሆን እንዳለባቸው ተመላክቷል፡፡

ከጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ገንዘብ ቅጣትና ከባድ የሚባል እርምጃ ድረስ በረቂቅ ደንቡ ተጠቅሷል፡፡በዚህም መሰረት አጭር ቀሚስ አስለብሶ የመስተንግዶ ስራ ሲያሰራ የተገኘ የሆቴል ተቋምም ሆነ መሰል አገልግሎት ሰጪ እስከ 50 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚያቀጣ ወ/ሮ ገነት ጨምረው ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡በሌላ በኩል ከጌጣ ጌጥ ጋር ተያይዞ ጆሮ ላይ ከአንድ በላይ ጌጥ አድርጎ መገኘትን ረቂቅ ደንቡ ይከለክላል ሲሉ ወ/ሮ ገነት ይመር ጨምረዉ ለብስራት ሬድዮና ቴሌቭዥን ተናግረዋል፡፡

በመመሪያዉ ላይ የቢሮዉ የቱሪዝም ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ መስተንግዶ ማህበር፣ የአዲስ አበባ ሆቴሎችና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማህበር፣ የቱሪዝም ማሰልጠኛ ተቋም እና የአዲስ አበባ ሆቴሎች ስራ አስኪያጅ ማህበር መሳተፋቸው ተመላክቷል፡፡ደንቡ በአዲስ አበባ ያሉ ሆቴልና መሰል ተቋማት ወጥ የሆነ ስርዓት እንዲሰፍን ከማገዙም በላይ ባህልና ወጉን ያልጠበቀ የአለባበስ ስነ-ስርዓትን በመቆጣጠር ኢትዮጵያዊ አለባበስና መስተንግዶ ስርዓትን ለማስከበር እና ባለሙያዎች ከሚደርስባቸዉ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጫናን ለማስቀረት አጋዥ ነዉ ተብሏል።

የወጣዉ ረቂቅ በአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ታይቶ በካቢኔ ከፀደቀ በኋላ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆና ተብሎ ይጠበቃል።ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቢሮዉ በተሰጠዉ ስልጣን መሰረት ያወጣዉን ደንብ ከፍትህ ተቋማት ጋር ሙሉ በሙሉ የማስፈፀም መብት እንዳለዉ ተጠቅሷል፡፡