Get Mystery Box with random crypto!

ዐበይት ዜናዎች 1፤ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከታጣቂዎች እገታ የተለቀቁ ሽፌሮችና ቤተሰቦ | ኢትዮ መረጃ - NEWS

ዐበይት ዜናዎች

1፤ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከታጣቂዎች እገታ የተለቀቁ ሽፌሮችና ቤተሰቦቻቸው መንግሥት በአጋቾች ላይ ርምጃ አለመውሰዱ እንዳስገረማቸው መናገራቸውን ቪኦኤ ዘግቧል። ሰኔ 10 ቀን ዓሊዶሮ በተባለ ቦታ ሹፌሮችና ረዳቶችን ጨምሮ በታጣቂዎች 79 ሰዎች ታግተው እንደነበር አንድ 500 ሺህ ብር ከፍሎ የተለቀቀ ሹፌር መናገሩን ዘገባው ጠቅሷል። በምሥራቅ ጎጃም ዞን ማቻከል ወረዳ አማኑኤል ከተማ ደሞ አንድ ታጋች በጉልት ንግድ የሚተዳደሩት አባቱ ቤታቸውን አስይዘው እንዳስለቀቁት ተናግሯል ተብሏል። እገታው በተፈጸመበት ቦታ በቅርብ ርቀት ላይ የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ እንደሚገኝ ታግተው የተለቀቁት ግለሰቦች መናገራቸውንም ዘገባው ጨምሮ ገልጧል።

2፤ ትናንት በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትና ውርጃን በማውገዝ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸውን ዶይቸቨለ ዘግቧል። የተቃውሞ ሰልፉን ያዘጋጁት፣ ሀዋሳ ከተማ ውስጥ የሚገኙ የፕሮቴስታንት እምነት ቤተክርስቲያናት እንደኾኑ ዘገባው እአመልክቷል።

3፤ በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ አንድ ታጣቂ የወረዳውን ፖሊስ አዛዥና ምክትላቸውን መግደሉን "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ዘግቧል። የፖሊስ አዛዡ ኢንስፔክተር ዘውዱ ታደሠ እና ምክትላቸው ወርቁ ሽመልስ የተገደሉት የ8ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና አሰጣጥ ጸጥታ ኹኔታን ለመመልከት አባይ ሸለቆ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት በተሽከርካሪ ሲጓዙ እንደኾነ የወረዳው ኮምንኬሽን ቢሮ መናገሩን ዘገባው አመልክቷል። የፖሊስ አዛዦቹ ሹፌር በጥቃቱ ቆስሏል ተብሏል። የወረዳው ጸጥታ ኃይሎች ገዳዩን ለማፈላለግ ባካባቢው እንደተሠማሩ ተገልጧል።

4፤ ዓለማቀፍ የፍልሰት ድርጅት የመንና ጅቡቲ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወሰዷቸው ርምጃዎች ከአፍሪካ ቀንድ ወደ ባሕረ ሰላጤው የሚደረገውን የፍልሰተኞች ጉዞ ባለፈው ግንቦት ብቻ በ15 በመቶ እንደቀነሰው ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል። የየመን ጸጥታ ኃይሎች በቅርብ በሕገወጥ ፍልሰተኞች መተላለፊያ ላይ የወሰዱት ርምጃ ሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎችን እንዳስበረገጋቸው ዘገባው ጠቅሷል። ከሱማሊያ ወደ የመን የሚገቡ ፍልሰተኞች ብዛት ግን በዚያው ወር ከ70 በመቶ በላይ መጨመሩን ድርጅቱ ገልጧል።. [ዋዜማ]

@ethio_mereja_news
@ethio_mereja_news