Get Mystery Box with random crypto!

አጫጭር ዜናዎች 1፤ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ምክር ቤት የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የ | ኢትዮ መረጃ - NEWS

አጫጭር ዜናዎች

1፤ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ምክር ቤት የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የአሜሪካ ዓለማቀፍ ተራድዖ ድርጅት በትግራይ ክልል ያቋረጡትን የዕርዳታ ሥርጭት እንዲቀጥሉ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። ምክር ቤቱ ከትግራይ የዕርዳታ እህል መዘረፉን ማረጋገጡን ገልጦ፣ "የዕርዳታ ሥርጭት ተቋርጦ መቀጠሉ ግን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል" ብሏል። ምክር ቤቱ፣ ፌደራልና የክልሉ መንግሥት በዕርዳታ ዝርፊያው ላይ ምርመራ አድርገው አጥፊዎችን ተጠያቂ እንዲያደርጉም ምክር ቤቱ አሳስቧል። ሁለቱ ድርጅቶች ባለፈው ወር የዕርዳታ ሥርጭት ያቋረጡት፣ በክልሉ የዕርዳታ እህል ተዘርፎ ገበያ ላይ እንደተሽጠ ደርሰንበታል በማለት ነበር።

2፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ "የኤርትራ ሠራዊት የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ስምምነት ተቆጣጣሪ ሥራን እያደናቀፈ ነው" በማለት መክሰሳቸውን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል። ጌታቸው ይህን የተናገሩት፣ በሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ዙሪያ ለተቆጣጣሪ ቡድኑ በሰጡት ገለጻ መኾኑን ዘገባው ጠቅሷል። የተቆጣጣሪ ቡድኑ ሃላፊ ሜጀር ጀኔራል ስቲፈን ራዲና፣ ቡድናቸው ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውጭ ሌሎች ኃይሎች ይኑሩ አይኑሩ ለማጣራት በቀጣዩ ወር ደቡባዊና ምዕራብ ትግራይን እንደሚጎበኝ መናገራቸውን ዘገባው ጨምሮ አመልክቷል።
 
3፤ ዓለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግሥት ለአገሪቱ ችግሮች ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን የሚያሰፍኑ መፍትሄዎችን እንዲያመጣ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። በመላ አገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለ መኾኑን የገለጠው ባንኩ፣ የሰላም ግንባታ፣ የእርቅና ዘላቂ ልማት መርሃ ግብሮችን መደገፉን እንደሚቀጥል ገልጧል። ባንኩ ድጋፍ የሚደግፋቸው ዘርፎች፣ የሁሉንም ሕዝብ ፍላጎቶች የሚመልሱ ስለመኾናቸውና ከመድልዖ የጸዱ፣ በሕዝባዊ ምክክርና አሳታፊነት ላይ መመስረታቸውን፣ የንብረት ባለቤትነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት መስፈኑን በቅድሚያ እንደሚያረጋግጥ አመልክቷል። ባንኩ እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ የምግብ ዋስትና፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ፣ ሴቶችን ማብቃትና የማኅበራዊና የአካባቢ ጥበቃ የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን በማገዝ ላይ እገኛለኹ ብሏል።

4፤ ዘንድሮ ከጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ወደ ብሄራዊ ባንክ የገባው የወርቅ ምርት በከፍተኛ መጠን መቀነሱን ዶይቸቨለ ዘግቧል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር፣ ከቤንሻንጉል ለባንኩ የገባው ወርቅ በ1 ሺህ 400 ኪሎ ግራም እንዲሁም ከጋምቤላ የገባው በ900 ኪሎ ግራም መቀነሱን ዘገባው አመልክቷል። ከሁለቱ ክልሎች የሚገባው ወርቅ የቀነሰው፣ የሕገወጥ ንግድ በመስፋፋቱ እንደኾኑ ተገልጧል። መንግሥት የወርቅ ሕገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር በቅርቡ ግብረ ኃይል ማቋቋሙ ይታወሳል።

5፤ በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ጠቅላላ ጉባኤው ተስተጓጉሎበት የነበረው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በቀጣዩ ዕሁድ የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤውን ሊያካሂድ መኾኑን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን የሚያካሂደው፣ በኢትዮጵያ ሆቴል አዳራሽ መኾኑን ገልጧል። ምርጫ ቦርድ ባልደራስና እናት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔያቸው በጸጥታ ኃይሎች መሰናከሉን አውግዞ፣ የራሱን አዳራሽ ለፓርቲዎቹ እንደሚፈቅድ ገልጦ ነበር። [ዋዜማ]

@ethio_mereja_news
@ethio_mereja_news