Get Mystery Box with random crypto!

በክልሎች የሚካሄደው የሽግግር ፍትሕ ምክክር መድረክ ከሚያዝያ እስከ ነሐሴ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚ | ኢትዮ መረጃ - NEWS

በክልሎች የሚካሄደው የሽግግር ፍትሕ ምክክር መድረክ ከሚያዝያ እስከ ነሐሴ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ ተገለጸ

በክልሎች የሚካሄደው የሽግግር ፍትሕ ምክክር መድረክ በ58 ከተሞች ከሚያዝያ እስከ ነሐሴ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ የፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ ሲስተዋሉ ከቆዩ ችግሮች በመነሳት ሙሉ ፍትሕ የሚሰጥበት፣ ዘላቂ ሰላም፣ እርቅና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አውስቷል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ስርዓትን ስኬታማ ለማድረግም ሒደቱን በተሟላና በተቀናጀ መልኩ ለመተግበር የሚያስችሉ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸው ነው የተጠቆመው፡፡

በዚህ ረገድ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማርቀቅ ስራ ለመጀመር የሚያስችለው የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አማራጮች መነሻ ሰነድ ሚኒስቴሩ ባደራጀው ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን መጠናቀቁ ተጠቅሷል፡፡ በክልሎች ደረጃ የሚካሄደው ምክክር በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ 58 ከተሞች ከሚያዝያ እስከ ነሃሴ 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለማከናወን መርሐ ግብር መውጣቱ ተገልጿል፡፡

የመጀመሪያ ምዕራፍ በቅርቡ በአዳማ ከተማ የተካሄደ ሲሆን ÷በዚህም ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች የሚወክሉ ግለሰቦችና ባለድርሻ አካላት በከፍተኛ ንቃት እና የባለቤትነት ስሜት ተሳትፈዋል፡፡ በመድረኩ የፖሊሲ አማራጭ ሰነዱን ለማዳበር የሚያስችል ሰፊ ግብዓት የማሰባሰብ ስራ መከናወኑም ተጠቁሟል፡፡

መድረኩ በቀጣይ ሁለት ሣምንታት በ15 የተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እንደሚካሄድም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

@ethio_mereja_news
@ethio_mereja_news