Get Mystery Box with random crypto!

.........የሳሚ ደብዳቤዎች........ ክፍል....1 | ልብወለድ Ethio_Fiction

.........የሳሚ ደብዳቤዎች........

ክፍል....1
ቀን 7/05/1997ዓ.ም

ፀኃፊ: ሳምሶን (የቻናሉ Admin)

ላኪ: ሳሚ
ተቀባይ: ራሂ

(የላኩልሽን ደብዳቤ ሌሊት ተነስተሽ እንድታነቢ በማሳሰብ ፃፍኩልሽ)

በተወደዱ ፊደላትና በተዋቡ ቀለማት
በልቤ ብራና ላይ የሳልኩት መልክሽን እንዳላስታውስ አድርጌ ያጠፋሁት መስሎኝ ነበር ። ይኸው ዛሬም መንግስታትን አየዘለለ ... ከብዙ ዓውደ ዓመቶች በኋላም እያንዳንዷን ሌሊት አንቺን ሳላሰላስል እነዚያን ምርጥ ቀኖች ያላንቺ እንደማላነጋ ... የሚወድሽ ልቤ አፅናኝ የራቃት ነፍሴ ... ትንገርሽ። በእነዛ ምትሃተኛ ቃላት እየቀመምኩ ስፅፍልሽ የነበሩ በጉጉት የምትጠብቂያቸው
ግጥሞች ትዝ ይሉሻል ... ?

እኔ ምልሽ ቃላቱ እንዴት እንደሚፈበረኩልኝ እስከዛሬ ግራ እጋባለሁ። በስሜት ያስሩኛል ... በተመስጦ የማልረግጠው ስፍራ አልነበረም... ከሰው ጋርም ሆኜ ብቻዬን ነኝ ግን አንቺ የቃላት ምንጬ እንደሆንሽ ታውቂ ነበር?

ይልቁኑ እኔን ስትጠሪኝ በሙሉ ስሜ አልነበረም። "ሳዬ" ነበር የምትይኝ ከዛም አልፎ "ሳ" ትይኛለሽ። ቆይ ግን "ስሜን እንደዛ የምታሳጥሪልኝ ለምን ይሆን?" ብዬ ስጠይቅሽ "ጊዜው ሲደርስ እነግርሃለሁ።" አልሺኝ። ጊዜው ስላለፈ
ደብዳቤዬ እንደደረሰሽ ምክንያትሽን በመልዕክተኛ ፅፈሽ በቶሎ ብትልኪልኝ ደስታዬ ወደር አልባ ይሆናል።

ደግሞ ያንቺ ጦስ የማያመጣብኝ ጣጣ የለም ... በቫላንታይን ሰሞን ... የገጠመኝን ላጫውትሽ ... ነገርግን አብዝተሽ መሳቅም ሆነ ማዘን አልፈቀድኩልሽም

ማምሻዬን ከስራ በመውጣት እግሬ እንዳመራኝ በከተማው መሀል ካለ ካፌ ውስጥ ጎራ አልኩኝ። ቤቱ በደማቅ እና የተለያዩ ቀለማትን በሚተፉ መብራቶች አጊጧል። ለናቷም ላባቷ የቀረች የምትመስል ቦታ አገኘሁና ወንበር ስቤ አረፍ አልኩኝ። ከእኔ በቀር ሁሉም ማለት ይቻላል ጥንድ ጥንድ ሆነው፣ አፍለአፍ ገጥመው ካፌውን አድምቀውታል። ለሰርግ የተጠሩ ሚዜዎች ይመስላሉ እንደውም ሙሽራው የታል እንድል አስገደዱኝ።

በነገሩ በመገረሜ ያዘዝኳትን ያመጣችልኝን ቀጭን አስተናጋጅ "የኔ እህት ሲንግሎች የት እንሂድ?" ብዬ ብጠይቃት። ብርጭቆዎቹን እያስቀመጠች በፈገግታ " እስቲ ከበስተኋላህ ዞር ብለህ ዕድልህን ሞክር።" ብላኝ ሂሳብ ሂሳብ ወደ ሚሏት ሰዎች ተፈተለከች። "ሲምቢሮ!" አልኳት በሆዴ።

አፍታ እንደቆየሁ የመጣልኝን የብርቱካን ሻይ ፉት አልኩና ሁኔታው ከንክኖኝ ከበስተኋላዬ ገልመጥ ሳደርግ እንደመደንገጥም እንደመሳቅም ያደረገችኝን አንቺን መሳይ ቆንጆ በኩራት ሆና አየሁ። ያውም ከዚህ ቀደም ሰርግ ላይ ሆነሽ የተነሳሽው ፎቶ ላይ የለበስሽውን ቀሚስ ራሱን ለብሳለች።

ልጂት እንዳየችኝ ምንም ሳይመስላት ስልኳን አንስታ መነካካት ቀጠለች። "አይ ዕድሌ ሲምቢሮ! ታይቷታል" በውስጤ ፈገግኩኝ። "ዛሬማ የቃላት ጥይት ያልቃል እንጂ አንላቀቃትም ዛሬማ ድባቅ መምታት አለብኝ።" ራሴን አጀገንኩት።

ከወንበሬ በዝግታ ተነሳሁ ፊቴን ወደ ኮራችው ውብ ልጅ ትይዩ አስተካከልኩኝ። ደሞ ሃይ ኮፒሽ እኮ ናት። አቤት መመሳሰል "ለሴት ልጅ ጀርባ አይሰጥም በሚል ብሒል ነው ወንበሬን ወዳንቺ ያዞርኩት።" አልኳት የልቤን መደለቅ ለመሸሸግ ጉሮሮዬን እየሳልኩ።

"ካልተሳሳትኩ ሙሽራዋ አንቺ ነሽ ።" አየኋት የልቧን ተራሮች ከናድኩት በሚል ፈገግታ።

" ታውቀኛለህ!?" ተኮሳተረች ።

" እሱን በሂደት " ዙሩን አከረርኩት።
ፊቷ መቅላት ጀመረ ... ድል በጠላት አቅጣጫ እያሽቃበጠች ሄደች...
አጠገቧ ለመቀመጥ እያኮበከብኩ የመጨረሻውን መድፍ ተኮስኩኝ።

"ብቻሽን ነሽ ማለት.. " አላስጨረሰችኝም።

"አፍህን ዝጋ! ደፋር!" ጮኸኝ።

ውሃ በላኝ ... ከባድ መኪና እየሄደብኝ ያህል ተሰማኝ በዙርያዬ ያሉ አፋቸውን ይዘው መሳቅ ጀመሩ።

ወረረኝ!

አቀረቀርኩ!

ባቀረቀርኩበት ....

"ወይኔ ሳዬ የኔ ናፍቆት..."

መብረቅ የሆነብኝን ድምፅ ሰማሁ ... ስድቧ ፕራንክ መሆን አለበት ማለት ነው። ተስለመለምኩ ተሽኮረመምኩ ... በደስታ ጨበስኩኝ አይ ራሂ ለኔ ብላ ካዲስ አበባ መጣች ውስጤን ማመን አልቻልኩም።
በፈገግታ ቆማለች፤ ተከትያት ቆምኩኝ።

አንድ ግዙፍ ለመሬት የከበደ ሰው ጥቁር አምባሳደር በነጭ ሸሚዝ የለበሰ ሽክ ብሎ ከበስተኋላዬ ወደ እርሷ ጎምለል ጎምለል እያለ መጥቶ ተጠመጠመባት።
እግዚኦ!

ቆሜ ቀረሁ!

ተቀመጥኩኝ
ዳግም አቀረቀርኩ ባቀረቀርኩበት ህመሜ ተነሳ .... ውድ ራሂ ስከፋም ስደሰትም ሙሉ ነገሬን በግጥም መግለፄን ላንቺ ማውጋት ለቀባሪ እንደማርዳት እንደሆነ የታመነ ነው።

ግጥም ግጠም አለኝ ....
ወረቀት አወጣሁ ... "ደግሞ ለጥቂት ሰንኝ ወረቀት ላውጣ አዎን ያው ይሁን እሺ።" ከገዛ ራሴ ጋር ንግግር ቀጠልኩ።
ማበዴ ነው አለች ዘፋኟ።

መፃፍ ጀመርኩ ...
ከንቱ ዕድሌ ጠማ ፊት አዙር ብላኝ
አይቀጡ ተቀጣሁ ፊት አዙሬ ብገኝ
ቀጠልኩ...
ስም ያለው ሞኛሞኝ እንኳንም ተሞኘ
እበላለሁ ብሎ ሲበላ ተገኘ
ቀጠልኩ... ➷(በ ይጠብቃል)
ማን አፍቅር አለው
ማን ውደድ አለው
ይፃፍ ይጫር እንጂ ገጣሚ ምናባቱ
ጨለማ ናት ሚስቱ ምሽግ ናት እቤቱ።

ሂሳቤን ከፍዬ መልሴን ሳልጠብቅ ተፈተለኩ! አይ ዕዳዬ

ያንቺው ሳ!

ቸር ያገናኘን!
ከሰላምታ ጋር
~ተፈፀመ~

ቀጣይ ፅሁፎቼን እንዲደርሳችሁ
ይቺን ተጫኑልኝ

Share ---> @ethio_fiction