Get Mystery Box with random crypto!

#ርዕስ :- 'እነ ሙጢ ጋ እየሄድኩኝ ነው' #ክፍል :- ሁለት ...መሄድ የፈለገችው ወደ ሃያ | ልብወለድ Ethio_Fiction

#ርዕስ :- "እነ ሙጢ ጋ እየሄድኩኝ ነው"

#ክፍል :- ሁለት

...መሄድ የፈለገችው ወደ ሃያ ሁለት ስለሆነ፣ ቶሎ የሚገላገልበትን  መንገድ መርጦ መምዘግዘግ ጀመረ።
“አባቱ!... በሀያ አራት ልትሄድ ትችላለህ” ስትለው በድጋሚ ተበሳጨ። መጓዝ ከጀመሩ በኋላ አቅጣጫ የሚለዋውጡ ወይንም “እግረ መንገድህን እንትን ጋር  ቆም ታደርግልኛለህ” የሚሉትን አይወድም። ከሁሉ የሚጠላው ግን “ገንዘብ ይዘውልኝ እስኪመጡ…” ብለው ከደረሱ በኋላ የትዕግስቱን መንገድ እንደገና ወዳላሰበበት አቅጣጫ የሚነዱትን ነው። በራይድ ስራ ላይ ብዙ የሚገርሙት ነገሮች አሉ። ለግርምቱ መጠን ተወዳዳሪ የሚያጣለት ግን… ሁሉም ተሳፋሪ የሚሄድበትን አድራሻ ከስም በስተቀር ያለማወቁ ታኢብ ነው። የሚሄዱበትን እሱ እንዲያውቅላቸው የሚፈልጉት ነገር…።

ተሳፋሪዎቹ ይገቡታል። ወሬ የሚፈልጉ እና የማይፈልጉት ብሎ ይከፍላቸዋል። የወሬ መነሻው “ስራ እንዴት ነው?” የሚል ነው። እሱን ሲመልስ… “በቀን ስንት ታገኛለህ?” ይከተላል። ይከታተላል። “መኪናው ያንተ ነው ወይስ… ለገቢ ነው የምትሰራው?”
በተቻለው መጠን ፊቱን ቅጭም አድርጎ ገና ከመነሻው “ጥያቄ አልፈልግም” የሚል ማስታወቂያ ይሰራል። ግን ከፋይ ስለሆኑ የሱን ፊት መልዕክት ቢያውቁም፣ በራሳቸው ፍላጎት እሱን ባሪያ አድርገው የሚቀጥሉ ይበዛሉ። የሱን ያለማድመጥ ፍላጎት በራሳቸው የማውራት ፍላጎት ይገለብጡታል።  የባጥ የቋጡን አውርተው ተንፈስ ብለው ይወርዳሉ። እንደ ልብ ጓደኛ ሚስታቸውን የሚያሙለት አሉ። ልክ እመውረጃቸው ሲደርሱ በቅጽበት ባዳ ይሆናሉ።

በወሬ ያጋሉትን ጆሮውን መልሰው ባይተዋር አድርገው ፍሪጅ ይከቱታል። ያንን ሁሉ አውርተው “በቃ እዚህ ጋ” ብለው ሲያዙት ሌላ ሰው ሆነው ነው። “አላውቅህ አታውቀኝ” የሚለው የመለያያ ዜማ፣ ድምጽ አልባ ሆኖ የመኪናውን ድባብ ይቆጣጠረዋል።
መጀመሪያ ሰሞን…ገና ለሥራው አዲስ እያለ… ካደረሰው ሰው ሁሉ ጋር ዝምድና የመሰረተ ይመስለው ነበር። “ለስራ ከፈለጋችሁ ስልኬን ሴቭ አድርጉና ደውሉልኝ” ይል ነበር። ቲፕ የሰጠውን ከማመስገን አልፎ ይሳለም ነበር። በኋላ ቲፑን እየጠበቀ የመቋመጥ ልምድ ሲጠናወተው በራሱ አፈረ። ከተቻለ እቅጩን ለመቀበል እንጂ አልፎ የሚመጣውን በመጠበቅ መቁለጭለጭ እርም ብሎ ተወ። መጣ ቀረ ብዙ ለውጥ አያመጣም። ለማይረባ ነገር ሱሰኛ መሆን ነው ትርፉ። እንዲያውም አንዳንዴ ዝርዝር የለንም ሲሉ ይተውላቸዋል። ዝርዝር በመፈለግ የሚባክነው ጊዜ ይባስ ያበሽቀዋል። እስከ ሀያ ብር ድረስ የራሱን ጥቅም አሳልፎ ይሰጣል።

ከሀያ ብር በላይ ግን “አሁንስ በዛ” ብሎ ያበሳጨዋል። እሩብ  ጉዳይ ነገር ነው አቋሙ። እሩብ ጉዳይ ከሙሉው ክፍያ ቢጎድል ችግር የለውም። ግማሽ ካሉት ግን አሻፈረኝ ይላል።
እቺኛዋ ግን ግማሹን እንኳን ከሰጠችው አመስጋኝ ነው። ልክ አሮጊት አሳፍሮ እንደማድረስ በመሰለ አኳኋን። የሆነ በምድር ሳይሆን በሰማይ የሚከፈል አይነት ስሜት የሚሰጥ አገልግሎት አለ። እቺኛዋ ለሰማይ እድሜዋም ማንነቷም አያቀራርባትም። ምናልባት ያቀፈችው ህጻን ሌላ ሚዛን ላይ ካላስቀመጣት በስተቀር። ህጻን ታቅፈው እንደሚለምኑት የምስኪንነት ደረጃ ያስጠጋት ይሆናል። ጠቅልላ የታቀፈችው ህጻን መሆኑም ግን ያጠያይቃል። ህጻኑ ሽታም ለቅሶም የለውም።