Get Mystery Box with random crypto!

ጠበኛ እውነቶች ደራሲ:- ሜሪ ፈለቀ 'እናትሽ በጠና ታማለች። እባክሽ ልታይሽ ትፈልጋለች።' ለአ | ልብወለድ Ethio_Fiction

ጠበኛ እውነቶች
ደራሲ:- ሜሪ ፈለቀ

"እናትሽ በጠና ታማለች። እባክሽ ልታይሽ ትፈልጋለች።"
ለአራተኛ ጊዜ የተላከልኝ መልዕክት ነው።

"እስካሁን አልሞተችም እንዴ? ለምን ታጓጓኛለች? አንዳችሁ እንኳን ምናለ ‘ሞተች’ የሚል ብስራት ብታሰሙኝ?"

"በስመ አብ ወ ወልድ ወ መንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ!! (ገዳዳ መስቀል በሰራ እጁ እያማተበ) ምነው ልጄ? ምን የሚሉት ጭካኔ ነው? ደግም አይደል! እግዜርም አይወደው።"

መልሴ አንገሽግሾታል። ሀምሳ ዓመት የሚያልፈው ሰውዬ ነው። የወለደችኝ ሴትዮ የነፍስ አባቷ ነው።

"በናትህ ከቤቴ ውጣልኝ!!"

"ምነው ልጄ? እግዜር የሰጠኝን ሹመት ባታከብሪ በእድሜ አባትሽ አልሆንም?" የሚናገረው ቃል የለዘበ ይሁን እንጂ ቀይ ወጥ የመሰለ ግለታም ዓይኑ እንደተጠየፈኝ ያሳብቅበታል።

እድሜውን ሳይሆን የለበሰውን የቤተ ክህነት ልብስ ባከብር ደስ ባለኝ ግን ለባሹ ልብሱን እንጂ ልብሱ ለባሹን እንዴት ሊያስከብረው ይችላል? ልብሱ ይሄን ከንቱ ሰውዬ እንዴት ክቡር ሊያደርገው ይችላል? መሆን የነበረበት ልብሱ ተገፎ ለተከበረ ሰው መደረብ ነበር። ያኔ ልብሱም ለባሹም ይከበራሉ።

መጎናፀፊያ አካልን ይሸፍን ይሆናል፤ ምናልባትም የአካል እንከንን የነፍስ ሴሰኝነት ግን በልብስ አይሸፈንም። ዝቃጭ ምግባር ግን ለቅድስና ሌት ተቀን ለሚታገሉ ልበ ብርቱዎች በተዘጋጀ መደረቢያ አይከለልም። በሱ ቤት እኔ ከእናቴ ጋር የሚሰራውን ብልግና አላውቅበትም። የናቴ ውሽማዋ ነው።

ይሄኔ በየመቅደሱ ‘ሰው የዘራውን ያጭዳል’ እያለ ይቦጠለቃል። እሱ ግን ያልዘራውን ለማጨድ በሰው እርሻ ይኳትናል።

ሴሰኝነትን እየዘራ መከበርን ለማጨድ ማጭድ ይስላል። ከንቱ!!

ይሄኔ ስንቶች ስንጥር ለምታክል በደላቸው ንሰሃን ሽተው ከፊቱ ሲመጡ ዋርካ የሚያክል ስድነቱን በብብቱ ሸሽጎ ልባቸው ለንሰሃ እንዲሰበር ዘክሯል። የዘቀጠ!! የእናቴን ጣር ላይ መሆን ሊነግሩኝ እንደመጡት ሶስቱ እሱም
እየተፀየፈኝ ቤቴን ለቆ ወጣ።

(ከመፅሃፉ ገፆች የተቆረሰ)

#share -----> @ethio_fiction

#comment ---> @Cr7_reunited