Get Mystery Box with random crypto!

የሳንካራ ስም ዛሬም ድረስ ለምን ተደጋግሞ ይነሳል ? ቶማስ ሳንካራ ምድር ላይ ለ37 ዓመታት ብ | ልብወለድ Ethio_Fiction

የሳንካራ ስም ዛሬም ድረስ ለምን ተደጋግሞ ይነሳል ?

ቶማስ ሳንካራ ምድር ላይ ለ37 ዓመታት ብቻ የተራመደ ነገር ግን በማእበል የማይጠፋ ዱካ አሳርፎ ያለፈ የዘመናችን አፍሪካዊ አብዮተኛ ነው።

በቅኝ ግዛት ወቅት "አፐር ቮልታ" ትባል የነበረችውን በርሀማ ደሀ ሀገሩን "ቡርኪና ፋሶ" ወደሚል ይፋዊ መጠሪያ የቀየረ፣ ተበታትነው ይኖሩ የነበሩትን ህዝቦቿን "ቡርኪናቤ" የተሰኘ የጋራ ማንነት እንዲጋሩ ያደረገ፣ ለዜጎቹ ህይወት የሚገደው ባለራዕይ መሪ ነበር።

ለምዕራባውያን ኃያላን ሀገራት ጫና ፍፁም ሳይንበረከክ በታደመባቸው ዓለምአቀፋዊና አፍሪካዊ ስብሰባዎች ላይ ሁሉ ዓለምን በማናለብኝነት ሲመዘብሩ ከነበሩ ሀገራት መሪዎች ጋር ጎሮሮ ለጎሮሮ ሲተናነቅ ያሳለፈ፣ ለጥቁር ህዝቦች እና በደል ላጎበጣቸው ምንዱባን ልሳን ሆኖ ያለፈ፣ ዓለም ከማይረሳቸው አብዮተኞች መካከል ጎልቶ የሚታወስ አፍሪካዊ እንቁ ነው።

"የራስን የተፈጥሮ ሀብት በራስ ጉልበት ማልማት" በሚለው የሀገሩን ህዝብ ባነቃነቀ ዘመቻ ያስመዘገባቸው አስደናቂ ድሎች አፍሪካ የራሷን ተፈጥሯዊ እድገት እንድታድግ ለማይፈልጉት ምእራባውያን ሀገራት እንደ ስጋት እንዲቆጠር አድርጎት ነበር።

ድሎት የማያሸንፈው ቆፍጣናው ወጣት ወደ ፕሬዝዳንትነት ከመጣ ጊዜ አንስቶ የቅንጦት ኑሮን ኖሮ አያውቅም። ከህዝብ ጋር የዩኒፎርሙን እጅጌ ከፍ አድርጎ ስሚንቶ የሚያቦካ፣ አካፋና ዶማ አንስቶ ጥቁር ላብ በግንባሩ እስኪንዠቀዠቅ ድረስ ሰርቶ የሚያሰራ፣ ድሆች ያለ ልኬት የሚሳሱለት መሪ ነበር።

አካሄዱ ባስፈራቸው ምዕራባውያን መሪዎች እና ስልጣን ባናወዛቸው የቅርብ ጓዶቹ በአጭር ቢቀጭም ተራማጅ ሀሳቦቹና ያስመዘገባቸው ተጨባጭ ለውጦች ዛሬም ድረስ ስሙ ተደጋግሞ እንዲነሳ አስችሎታል።

(ከሰለሞን ዳኜ - ቶማስ ሳንካራ ጥቁሩ አብዮተኛ)

@ethio_fiction