Get Mystery Box with random crypto!

የምስራቅ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ G+7 ግንባታን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል፡፡ የአዲስ | Ethiopian Construction Work Professionals - ETCONp

የምስራቅ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ G+7 ግንባታን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ በበጀት ዓመቱ እያከናወናቸው ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል የሚጠቀሰውና በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ስራው ተጓቶ የቆየው የምስራቅ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ G+7 ህንፃ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ ይውል ዘንድ የቢሮው ማኔጅመንት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ችግሮቹ ተፈተው ወደስራ በመመለስ ከውሳኔው በኋላ በነበረው 1 ወር በተሰሩ ስራዎች ፍሬያማ ውጤቶች በመመዝገብ ላይ ናቸው፡፡

በምስራቅ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ በ567.2 ሜትር ካሬ ቦታ ላይ ያረፈውና በቢ.ጂ.ኤም ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭነት እንዲሁም ኤ.ቲ.ኤም አርክትክቶችና ኢንጂነሮች አማካሪነት እየተገነባ የሚገኘው ይህ ባለ 8 ወለል ሕንፃ ባለፈወ 1 ወር በተሰሩ ስራዎች የሴራሚክ ወለል ንጣፍ ስራ፣የመጨረሻ ወለል የስርገት መከላከያና የሴራሚክ ስራ፣የሳኒተሪ ስራዎች፣የሴፕቲክ ታንክ ስራዎች፣የአርምስትሮንግ ኮርኒስ ስራዎች  እና ሌሎችንም ስራዎች ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ተቋሙ ምቹ የመማር ማስተማር ከባቢ ኖሮት አምራችና ስኬታማ ትውልድ ማፍራት በሚያስችለው የጥራት ልክ እንዲጠናቀቅ የህንፃው ውጫዊ አካል እጅግ ውብ እና ማራኪ ገፅታን የመፍጠር ዓቅም ባለው   Calla Contextra   የቀለም ቅብ ስራ በ5 እጅ  እየተከናወነለት የሚገኝ ሲሆን የግራናይትና የአልሙኒየም ስራዎችም ደረጃቸውን ጠብቀው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

የሳይት ስራ፣የሊፍት ገጠማ ፣የውሀ ፓምፕ ገጠማ፣የበር ገጠማ፣የመስኮት መስታወት ገጠማ፣የህንፃው የውስጥ ቀለም ስራ፣የጀነሬተር እና የመሳሰሉት ዋና ዋና ስራዎች በተያዘላቸው ዕቅድ መሰረት በቀጣይ የሚከናወኑ ይሆናል፡፡

በተቋሙ ከፍተኛ አመራር ያላሰለሰ ክትትል እየተደረገለት የሚገኘውና ሲጠናቀቅ በክህሎት፣በዕውቀት እንዲሁም በስነምግባር የላቀ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ማሕበራዊ ፋይዳ የሚኖረው ይህ ፕሮጀክት ከ1 ወር ባነሰ ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይውል ዘንድ በከፍተኛ ርብርብ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ቢ.ጂ.ኤም ኮንስትራክሽን ተመሳሳይ ንድፍ ያለውን የተግባረዕድ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አውቶሞቲቭ ዎርክሾፕ ከቢሮው ጋር በነበረው ውል መሰረት ባሳለፍነው በጀት ዓመት አጠናቆ ለአገልግሎት ማዋሉ የሚታወስ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

@etconp