Get Mystery Box with random crypto!

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ሙሉ በሙሉ ውድመት የደረሰበት የቆቦ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በ2015 የትም | ETHIO STUDENTS NEWS™

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ሙሉ በሙሉ ውድመት የደረሰበት የቆቦ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በ2015 የትምህርት ዘመን የተግባር ሥልጠና የሚያስፈልጋቸውን ትምህርቶች መስጠት እንደማይችል አስታወቀ።

ኮሌጁ የተግባር ሥልጠና የሚያስፈልጋቸውን ትምህርቶች ላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የማይችለው፣ በጦርነቱ የወደመውን የተግባር ሥልጠና መስጫ ማሽነሪዎች መተካት ስላልቻለ መሆኑን የኮሌጁ ዲን ደሳለኝ አደም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ኮሌጁ ከ79 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው 810 ማሽነሪዎች ሙሉ በሙሉ እንደወደመበት የገለጹ የኮሌጁ ዲን፣ ከአይሲቲ ትምህርት ውጭ የተግባር ት/ት ባለመስጠቱ በዓመት መቀበል ከሚችለው 1 ሺሕ 500 ተማሪ አሁን ላይ መቀበል የሚችለው 500 ተማሪ ነው ብለዋል።

ኮሌጁን ለማቋቋም ከክልል እስከ ፌደራል የተሰየሙ የመንግሥት ተቋሞች፣ በታቀደው ልክ ድጋፍ እያደረጉ አለመሆኑን ደሳለኝ ጠቁመዋል። መንግሥት የወደሙ ተቋሞችን መልሶ ለማቋቋም የትስስር ሥራ ቢፈጥርም በተግባር የሚታየው ድጋፍ አነስተኛ ነው ተብሏል።

የራያ ሰላምና ልማት ማኀበር ኮሌጁን ለማቋቋም ለኹለተኛ ጊዜ የኮምፒውተር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ ማኀበሩ ያደረገው ድጋፍ ኮሌጁ መልሶ ለማቋቋም መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር የሚያግዝ ነው ተብሏል።

ኮሌጁ ከዚህ ቀደም የተቀበላቸውን ተማሪዎች የተግባር ሥልጠና ሳይሰጥ ለተማሪዎች ሞራል ሲል ለማስመረቅ መገደዱን አስታውቋል። ኮሌጁ አሁን ላይ የመከላከያ ሠራዊት ካምፕ ሆኖ እያገለገለገለ ይገኛል።

ኮሌጁን መልሶ ለማቋቋም በትስስር የተመደቡ ተቋማትና መንግሥት እንዲሁም ባለሀብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ማኅበሩና ኮሌጁ ጠይቀዋል።

አዲስ ማለዳ
@ET_STUDENT_NEWS
@ET_STUDENT_NEWS