Get Mystery Box with random crypto!

' ክስ ከተመሰረተብኝ እመለሳለሁ! ' - አቶ ልደቱ አያሌው #Ethiopia | መንግሥት በ 'ሽ | ሰበር ዜና ET🇪🇹

" ክስ ከተመሰረተብኝ እመለሳለሁ! " - አቶ ልደቱ አያሌው
#Ethiopia | መንግሥት በ "ሽብር ወንጀል እጠረጥራቸዋል" ያላቸውን በውጭ ሀገር ያሉና ተላልፈው እንዲሰጡ ማዘዣ ካወጣባቸው ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆኑት ጉምቱው ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው "ክስ ከተመሠረተባቸው" ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመለሱ አሳውቀዋል።

አቶ ልደቱ እስካሁን ክስ እንዳልተመሠረተባቸው በጠበቃቸው እንደተነገራቸውና ክስ ከተመሠረተባቸው ግን ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመመለሱ ገልጸዋል።

ይህን የገለፁት ከቢቢሲ አማርኛ ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ ነው።

ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው ምን አሉ ?

"...ከጠበቃዬ ጋር እየተነጋገርኩ ነው። እስካሁን ክስ አልተመሠረተብኝም። ዝም ብሎ በራድዮና በቴሌቪዥን ይነገራል እንጂ የቀረበ ክስ የለም። ክስ ሲመሠረት ነው የምሄደው።

ክስ ከመመሥረቱ በፊት መሄዴ ጥቅም የለውም። በጊዜ ቀጠሮ መጉላላት ነው እንጂ ምንም ፋይዳ የለውም። እስከዚያ ድረስ ሕክምናዬን እከታተላለሁ /አቶ ልደቱ ለልብ ህመም በአሜሪካ የህክምና ክትትል ላይ ናቸው/ ።

ክስ ሲመሠረት ዳኞቹ የሚቀጥለው ሕክምናዬ ድረስ እንድቆይ የሚፈቅዱ ከሆነ እቆያለሁ። የማይፈቅዱ ከሆነም የሕክምና ቀጠሮዬን አቋርጬ እሄዳለሁ። "

አቶ ልደቱ ስለ ሽብር ክስ...

" የሕክምና ቀጠሮ ስለነበረኝ ነው እንጂ መጀመሪያም የመጣሁት እዚህ ለመኖር አይደለም። በቅርብ ጊዜ ወደ አገሬ እመለሳለሁ ብዬ እያሰብኩ ነበር። የዘገየሁት ያልተቋጨ የሕክምና ቀጠሮ ስለነበረኝ ነው። የሽብርተኛነት ክስ ሲመጣ ካሰብኩት ጊዜ ፈጥኜ ነው የምሄደው አልኩ።

የሕግ ተፈላጊነት ካለ፣በሽብርተኛነት የመጠየቅ ጉዳይ ካለ፣እኔ ከፍ/ቤት ውሳኔ እና ጥያቄ ርቄ መኖር ስለማልፈልግ ነው ለመሄድ የወሰንኩት።

...አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንጻር ተመልሼ ለመውጣት ችግር ሊገጥም ይችላል ብዬ ነው እስካሁን የዘገየሁት። አሁንም የሕክምና ቀጠሮ አለኝ። ግን የሕግ ተጠያቂነት ከመጣ ምንም ማድረግ አይቻልም።

የተከሰስኩበት ወንጀል በፍጹም ከእኔ ታሪክ እና ማንነት ጋር የማይሄድ ነው። ሥርዓቱ ደግሞ ይሄንን ያደረገበት የራሱ ምክንያት አለው። አንደኛው ምክንያት እንደዚህ ዓይነት ክስ ፈርቼ ወደ አገሬ እንዳልመለስ ለማድረግ ስለሆነ ይሄንን በፈቃደኛነት ለመቀበል ዝግጁ አይደለሁም።

እኔ ሰላማዊ ታጋይ ነኝ። ሁልጊዜም በሕግ ነው የምተማመነው። ካሁን ቀደምም አምስት ስድስቴ ታስሬ በፍርድ ቤት ነው ነጻ የሆንኩት። አሁንም በዚያ መንገድ ሄጄ የግድ ሥርዓቱን መጋፈጥ አለብኝ በሚል ነው የምመለሰው።

ማናችንም ላለመታሰር፣ ዋጋ ላለመክፈል የየራሳችን ምክንያት ይኖረናል። ትግል ሲባል ግን እነዚህን ሁሉ ነገሮች ጥሶ መከፈል የሚገባውን ዋጋ መክፈል ነው።

ወደኢትዮጵያ ሲገቡ ስለሚገጥማቸው ችግር...

" ስሄድ የሚገጥመኝ ችግር ቀላል ነው ብዬ አይደለም። ከባድ እንደሚሆን አምናለሁ። ያ ችግር ምናልባት ሕይወቴንም ጭምር የሚያሳጣ ሊሆን ይችላል።

ግን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ፣ ሕዝቡ ያለበት ሁኔታ፣ ሰዎች በዚህ ደረጃ ዋጋ ለመክፈል ካልተዘጋጀንና ካልከፈልን ይለወጣል የሚል እምነት የለኝም። በእኔ ደረጃ ያለ ሰው ያን ዋጋ መክፈል እና ለትግሉ አርአያ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ።

ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በፖሊስ ሊያዙ ስለሚችሉበት ሁኔታ...

" ልምዱ አለኝ። መታሰር የመጀመሪያዬ አይደለም። በዚህ ዓይነት ትግል ውስጥ ላለፉት 31 ዓመታት ቆይቻለሁ። ወደ 6 ጊዜ ስለታሰርኩ ለእኔ አዲስ ነገር አይደለም።

ከእኔ ጋር በመግለጫ የተጠቀሱ ግለሰቦች እየታደኑ እያተሰሩ እንደሆነ አውቃለሁ፤ ኤርፖርት የሚጠብቀኝ ፖሊስ እንደሚሆንና እንደምታሰር አውቃለሁ። ለዚህ የሥነ ልቦና ዝግጅት አለኝ።"
ቢቢሲ

@ET_SEBER_ZENA
@ET_SEBER_ZENA