Get Mystery Box with random crypto!

ስትኖር ለብቻህ አትኑር የሌሎችን ችግር በመፍታት ኑር ገንዘብ ካለህ በገንዘብህ ደሃውን በመርዳት | የቅዱስ ዮሴፍ እና የአሳይ ት/ቤት ግቢ ጉባኤ

ስትኖር ለብቻህ አትኑር

የሌሎችን ችግር በመፍታት ኑር
ገንዘብ ካለህ በገንዘብህ ደሃውን በመርዳት ኑር
ጉልበት ካለህ በጉልበትህ ደካመውን በመርዳት ኑር
እውቀት ካለህ እውቀትህን ሌላው በማካፈል ኑር
ሥልጣን ካለህ ለተበደሉት በመፍረድ ኑር
ቤት ካለህ ጎዳና ላይ ወድቆ የሚያድረውን ወንድምህን
በማስጠጋት ኑር
ልብስ ካለህ ራቁቱን ላለው ወንድምህ በማልበስ ኑር
ምግብ ካለህ የሚበለው ላጣው ወንድምህ በማብላት ኑር
ገንዘብ ካለህ ለሌላው አካፍል የአንተ ገንዘብ ባንክ
ተጨናንቆ ደሃ ሲቸገር እግዚአብሔር ይታዘብሃል
ጠንካራ ጉልበት እያለህ ደካማውን ወንድምህን ሳትረዳ
ስትቀር ጉልበት የሰጠህ አምላክህ ይመለከትሃል ጠንካራው
ጉልበትህ ደካማ ይሆናል አንተም በጊዜህ አንሱኝ ጣሉኝ
ትላለህ የአንተ ጠንካራ ጉልበት ደካማውን ለማሸነፍ አይደለም
የተፈጠረው ደሃውን ለመርዳት ነው እንጂ
እውቀትህ ሌላ ካላስተማርክበት እውቀቱን የሰጠህ ፈጣሪህ
እውቀትህን እንደሚነሳህ አስብ እውቀት ችግር መፍቻ ነው እንጂ
ችግር ማምጫ አይደለም እውቀት ወደብርሃን የሚመራ እንጂ
ወደጨለማ የሚወስድ አይደለም የአንተ እውቀት የዶክትሪት
የማስትሪት የድግሪ የዲፕሎማ የመጽሐፍ የቅኔ የድጓ የአቋቋም
የዝማሬ የቅዳሴ እውቀትህ ላላወቁት ለማሳወቅ እንጂ
ለመወደስ ለመከበር ለመፈራት አይደለም
በስልጣንህ የምታዳላ ከሆነ ሰማያዊ ስልጣን ባለው
ፊት ተከሰህ ስትቀርብ መልስ ታጣለህ ስልጣንህ ለተበደለ
ፈራጂ ለተቀማ አስመላሽ የድኀ እንባ አባሽ መሆን አለበት ዛሬ
ሰዎች ተከሰው ወደአንተ ፊት እንደቀረቡ ሁሉ አንተም ተከሰህ
በፈጣሪህ ፊት ትቀርባለህና
ልብስህ ቁም ሳጥን ሞልቶ ሻንጣ አጨናንቆ አንተ በሰላሳ
ቀን ሰላሳ ልብስ እየቀየርህ እንዳንተ ገላ ያለው ሰው ራቁቱን
ሁኖ ብርድና ሙቀት ሲፈራረቅበት የማታለብሰው ከሆነ ሰማይን
በደመና የሚያለብሰው ምድርን በእሳር የሚሸፍነው አምላክህ
ያዝንብሃል
አንተ ምን ልብላ ብለህ አማርጠህ ትበላለህ በቀን አራት
አምስት ጊዜ ትበላለህ እንዳንተ ምግብ የሚፈልገው ወንድምህ
የሚበለው አጥቶ ሲራብ ትተኸው ስትበላ በዝናብ አብቅሎ
በፀሐይ አብስሎ የሚመግብህ አምላክ የሰጠህን ምግብ
ይነሰሃል ታመህ ያየሀውን ሁሉ እንዳትበላ ያደርግሃል
ስትቆርጠው የነበረው ጮማ ስትጎነጨው የነበረው ውስኪ ሁሉ
ይቀራል
ገንዘብህ በባንክ እየደለበ ሌላውን ካረዳህበት ስትሞት
አብሮህ አይቀበርም ወደመቃብር ስትወርድ በአንድ ነጭ ነጠላ
ተጠቅልለህ ነው ሀብትህ ሁሉ አይከተልህም እግዚአብሔር
ሀብት የሰጠህ አንተ ለዳሀው ሰጥተህ እንድትጸድቅ ዳሀው
ተቀብሎ እግዚአብሔርን እንዲአመሰግን ነው
ሰው ሆይ በትክክለኛው መንገድ ኑር
ለኳስ ሁለት ሰአት ጊዜ ሰጥተህ ለቅዳሴ አንድ ሰአት
አልሰጠህም
ለፊልም ረጅም ጊዜ ሰጥተህ ለወንጌል አጭር ጊዜ አጥተሃል
ለኳስ ጨዋታ ተወራርደህ ብር ትሰጣለህ ለቤተ ክርስቲያን
ማሰሪያ እጅህ ይታሰራል
ለፊልም እስፖንሰር ትሆናለህ ለወንጌል ግን አምስት ሳንቲም
ለማውጣት ትቆረቆራለህ
የፊል አክተሮችን አንድ በአንድ ታውቃቸዋለህ የኳስ ኮከቦችን
በደረጃ ትጠራቸዋለህ
ወንጌሉን የጻፉት አነማናቸው ስትባል መልስ ታጣለህ
ሰው ሆይ አንተ ለዘለዓለም በምድር አትኖርም በሰማይ ለመኖር
የተፈጠርህ ነህ ወደምድር ያወረደህ የአባትህ የአዳም የናትህ
የሄዋን ኀጢአት ነው እንጂ ሀገርህ በሰማይ ነው ለተወሰነ ጊዜ
በምድር ትቆያለህ ሇላ ከምድር ወደላይ ትወሰዳለህ
በሰማይ በበጎ ቦታ ለመኖር በምድር ሳለህ መልካም ስራ ስራ
ከጎንህ የምታውቀው ሰው ሲሞት ከማልቀስ ባሿገር ነገ አንተ
እነደምትሞት ተማርበት ጎረቤትህ ዛሬ ሲሞት ነገ ተረው የአንተ
መሆኑን አትርሳ
ዓለም ጨለማ ናት ወደጨለማ ሳትወስድህ ወደብርሃን ተጉዘህ
ቅደማት የምታልፈው ዓለም እድሜህን በከንቱ ሳትጨርስብህ
ማለፏን አውቀህ ቅደማት ዓለም የዛሬ ናት ዛሬ አስደስታ ነገ
ታስለቅስሃለች
ዛሬ አሳይታ ነገ ታሳጣሀለች
ዛሬ አጥግባ ነገ ታስርብሐለች
ዛሬ ሹማ ነገ ትሽርሃለች
ዛሬ አክብራ ነገ ታዋርድሃለች
ዛሬ አሳምራ ነገ ታጠቁርሐለች
ዛሬ አድንቃ ነገ ትንቅሃለች
ዛሬ አጨብጭባለህ ነገ ድንጋይ ትወረውርብሐለች
ዛሬ ከፍ ከፍ አድርጋ ነገ ዝቅ ዝቅ ታረግሃለች
ለአንተ አባቶች አልሆነችም መቃብር ከታቸዋለች ከቀደሙት
አባቶችህ ተማር አባትህ የት? አለ መቃብር ውስጥ አይደል
እናትህ የት ?አለች መቃብር ውስስጥ አይደል የምታውቃቸው
ካንተ ቀድመው የነበሩ ዝነኞች ባለ ሀብቶች አርቲስቶች
የሃይማኖት አባቶች ባለ ስልጣናት ሁሉ መቃብር ውስጥ
እንደሆኑ ተረዳ
ስማቸው ከመቃብር በላይ ቀርቷል መልካም የሰሩት በመልካም
ስም ክፉ የት በክፉ ስም ይታወሳሉ
ሰው ሆይ ለሰው ችግር ሳትሆን ሰውን በመርዳት ኑር::