Get Mystery Box with random crypto!

አሸባሪው የህወሓት ቡድን አሁንም በአማራ እና አፋር ክልሎች በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች አለመውጣቱ | ESAT (ኢሳት🇪🇹)®

አሸባሪው የህወሓት ቡድን አሁንም በአማራ እና አፋር ክልሎች በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች አለመውጣቱን መንግስት አስታወቀ

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር በወረራ ከያዛቸው አካባቢዎች እንደወጣ ቢያወራም አሁንም በአማራ ክልል በወረራ ከያዛቸው አዲአርቃይ፣ ጸለምት፣ አበርገሌ እና ሌሎች አካባቢዎች እንዲሁም ከአፋር ክልል ደግሞ በራህሌ፣ ኮኖቫ፣ አብአላ፣ መጋሌ ወረዳዎች አልወጣም ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ የሰብዓዊ እርዳታ እና ሰሜኑን የኢትዮጵያን ሁኔታ በተመለከተ በሰጡት መግለጫ÷ መንግስት በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የክልሉን ነዋሪዎች ለመታደግ ሲባል የግጭት ማቆም ውሳኔን ተከትሎ በየብስ እና በአየር ትራንስፖርት የሚጓጓዘው የሰብዓዊ እርዳት ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡

የእርዳታ ፍሰቱንም የተሳለጠ ለማድረግ መንግስት ከእረጅ ድርጅቶች የሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎችን መፍታቱንም ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ሳምንትም የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ 165 ያህል የእርዳታ እህል የጫኑ ተሸከርካሪዎች መቀሌ መግባታቸው በመግለጫው ተነስቷል፡፡

መንግስት አቅም በፈቀደ መጠን የእርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ማቅረብ የሚችሉትን እርዳታ እንዲያቀርቡ ያላሰለሰ ጥረት ቢያደርግም÷ በአንጻሩ የትግራይ ወራሪ ኃይል የእርዳታ ማጓጓዝ ስራው እንዳይሳለጥ እንቅፋት እየሆነ ነው ብለዋል ዶክተር ለገሰ በመግለጫቸው፡፡

የእርዳታ እህል ለማሳለጥ ሲባል ከትግራይ ወጥተናል በሚል የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር የሚረጩት ወሬም መሰረተ ቢስ ነው ብለዋል፡፡

@Esat_tv1
@Esat_tv1