Get Mystery Box with random crypto!

ለቅዱሳን መዘመር ተገቢ ነውን? መፅሀፍ ቅዱስ ምን ይላል?? ፈጣሪ እንደ ልቤ ያለው ዳዊት የል | Ermi HD

ለቅዱሳን መዘመር ተገቢ ነውን? መፅሀፍ ቅዱስ ምን ይላል??
ፈጣሪ እንደ ልቤ ያለው ዳዊት የልቤን ማን እንደነገረው እንጃ የእኔን ጥያቄ ለመመለስ ቸኩሎ ጠበቀኝ፡፡ ገና የመጀመሪያው መዝሙሩን ‹‹ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሔደ ፣ በኃጢአተኞች መንገድ ያልቆመ ፣ በዋዘኞች ወንበር ያልተቀመጠ›› ብሎ ጀምሮት አገኘሁት፡፡ (መዝ. 1፡1) ዳዊት በዚህ ዝማሬው ‹ምስጉን ነው› ያለው ፈጣሪን ነው ወይንስ ፍጡርን? እግዚአብሔርን ነው እንዳልል ‹በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል› ይላል፡፡ ስለዚህ ዳዊት ዝማሬውን የጀመረው ‹በክፉዎች ምክር ያልሔደ ፣ በኃጢአተኞች መንገድ ያልቆመ ፣ በዋዘኞች ወንበር ያልተቀመጠ›ን ሰው በማመስገን ነው፡፡

ወደ መዝሙሩ ስገባ ዳዊት ምስጋናውን ሰፋ አድርጎ ‹ለቅኖች ምስጋና ይገባቸዋል› ‹ለችግረኛ የሚያስብ ምስጉን ነው› ‹አንተ የመረጥከው በአደባባዮችህም ለማደር የተቀበልከው ምስጉን ነው› ‹እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን ነው› ‹እልልታን የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው› ብሎ ከግለሰቦች አልፎ ሕዝብን ሲያመሰግን አገኘሁት፡፡ ከሁሉ ያስደነቀኝ ግን ‹‹መተላለፉ የቀረችለት ፣ ኃጢአቱ የተከደነችለት ሰው ምስጉን ነው›› የሚለው ዝማሬው ነው፡፡ ኃጢአቱን እግዚአብሔር ይቅር ያለውና በደሉን ፈጣሪ የሸፈነለት ሰው በታላቁ ዘማሪ በዳዊት አንደበት መዝሙር ከተዘመረለት በሃሳብዋ እንኳን ኃጢአትን ስላልሠራችው ድንግል ምን ዓይነት መዝሙር ይዘመርላት ይሆን?

ንጉሥ ዳዊት ሕይወት ላላቸው ሰዎች ብቻ ዘምሮ አላቆመም ፤ ለማትናገረውና ከእንጨት ከድንጋይ በሰው እጅ ለተሠራችው ከተማው ለጽዮን የእግዚአብሔር ማደሪያ በመሆንዋ ዝማሬን አዝንሞላታል፡፡
‹‹እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታል ፤ ማደሪያው ትሆነው ዘንድ ወድዷታል፡፡ እንዲህ ሲል ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት ፣ መርጫታለሁና በእርስዋ አድራለሁ››
‹‹እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል ፤ የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ በአንቺ የከበረ ነገር ይባላል››
‹‹በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን ፤ ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ አለቀስን ፤ የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን ፤ የእግዚአብሔርን ዝማሬ እንዴት በባዕድ ምድር እንዘምራለን? ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ፤ ባላስብሽ ምላሴ ከጉሮሮዬ ጋር ይጣበቅ ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ›› ብሎ ስለ ቅድስቲቱ ከተማ ሲዘምር አገኘሁት፡፡ ከራሱ አልፎም በዙሪያው ላሉት በመዝሙሩ እንዲህ ሲል ጥሪ አቀረበ ‹‹መዝሙረ ዳዊት 48
12፤ ጽዮንን ክበቡአት፥
በዙሪያዋም ተመላለሱ፥
ግንቦችዋንም ቍጠሩ፤ ›› የእግዚአብሔር ከተማ ጽዮንን ለማይወድዱ ደግሞ በመዝሙሩ ‹‹መዝሙረ ዳዊት 129
5፤ ጽዮንን የሚጠሉ ሁሉ ይፈሩ፥
ወደ ኋላቸውም ይመለሱ። ›› ብሎ ዘምሮአል፡፡

ዳዊት ስንት ኃጢአተኛ ሲራኮት ለሚውልና ለሚያድርባት ከተማ የእግዚአብሔር ማደሪያው እንድትሆን እንደ መረጣት አውቆ እንዲህ ሲዘምር ማየቴ ‹መንፈስ ቅዱስ ይጸልልሻል የልዑል ኃይልም ያድርብሻል› ለተባለችዋ ቅድስት ድንግል ማርያም ‹የጌታዬ እናት ፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ፣ የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ› ብዬ ለመዘመር እንድችል ኃይል የሚሠጥ ሆነልኝ፡፡ ባቢሎን በተባለ በኃጢአት ሥፍራ ሆኜ ድንግልን ባሰብኳት ጊዜ እንዳለቅስና ‹‹ድንግል ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ባላስብሽም ምላሴ ከጉሮሮዬ ይጣበቅ›› ብዬ እንድዘምርላት ድፍረት ሠጠኝ