Get Mystery Box with random crypto!

“ይድረስ ለፈጣሪ ባለህበት” ከባሪያህ ይሁኔ ኤፍሬም ካሳሁን “እንደምን ከ | Yihune Ephrem Kassahun

“ይድረስ ለፈጣሪ ባለህበት”
ከባሪያህ ይሁኔ ኤፍሬም ካሳሁን

“እንደምን ከርመሀል እንዳልልህ የምታሳምም እንጅ የምትታመም አይደለህም፡፡ ደህና ነኝ እንዳልልህ ደህንነቴን ታውቃለህና አልደክምም፡፡ አንተ እኔ ምን እንደበላሁ፤ ምን እንዳማረኝ፤ መቼ ከሀገር አፍራሾች ሊስት ውስጥ እንደምገባ ታውቃለህ እኔ ግን አንተ ዘንድ ምን እየተፈጠረ እንዳለ ለማወቅ እጓጓለው ሠው ደካማ ነውና እንደጓጓው አለው እንጂ ያ ቀዩ መላኢክትህ መጥቶ መች ነገረኝ ብለህ፡፡


አምላክ ሆይ መንግስት ሰማያት እንዴት ነች “መንግስተ ሠማያት ቀርባለች እና ንስሀ ግቡ” እየተባለ እየተለፈፈ ባለበት ዘመን ስንቱ ከንስሃ በፊት በጅምላ ወደአፈር እንደገባ ታውቃለህ? እናስ ምነው መዘግየትህ ወይንስ እዛው የኢትዮጵያ እስር ቤቶች ሠብሠብ ብለን እንድንጠብቅህ ከጀልክ እንደሱ ካሠብክ መልካም በቅርቡ መምጣትህ አይቀርም!!!

ሲኦልስ እንዴት ናት ገሐነብ ውስጥ የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች ብዙ ሠው ገዳይ እኔ ነኝ የሚል ግብግብ ጀምረዋል አሉ ያናድዳል አንተም አናደኸኛል፡፡ መቼም አንተ ሁሉንም ነገር ተቆጣጣሪ ነህና በመናደዴ……. ባትቆጣኝ የምልህ ነገር አለኝ፡፡

ከዚህ እኔ ካለሁበት መንደር ያሉ ዲያቢሎስን ከሰማየ ሠማያት ወደምድር ስትወረውረው ምስራቅ አፍሪካ ነው ያረፈው እያሉ ያማሉ ኧረ እንዳውም ኢትዮጵያ ነው ይላሉ፡፡ እኔ ግን አልኩኝ ይሁና አንተ ሀያል ነህና ሣጥናኤል ቢያስቸግርህ ወደምድር ሠደደክው ወረወርከው እኛስ በሀገራችን ያሉ ሣጥናኤሎችን ወደየትኛው ህልቁ እንወርውራቸው፡፡ እኛ ጠዋት ማታ እንደድኩላ በስጋት መሸማቀቁ ሰልችቶናልና ይህን የተንኮል ማማሠያ የሚሰሩትን ሁሉ፤ ጥበባቸውን ድፍን አድርግባቸውና እኛም እንደልባችን ተንፈራጠን እንቀመጥ፡፡

አሁን እኮ መቼም ያለብን ስጋት እንዲህ አይምሰልህ፤ ሊያውስ መቼ አጣኸውና እነግርሃለው አንዱ አንድ ሲሠራ ሌላው ሌላ ይሠራል፡፡ ይኸውም እንዲህ መላ ቅጡ ጥፍት ባለው መንደር ውስጥ እየማልን ለአንተ መስገዱን ትተን፣ ለመሳሪያው ሠሪዎች መስገድ ጀምረናልና እንዳትቀርብህ ለራስህ ስትል አስብበት፡፡ የፖለቲከኞቹ ራዕይ ከዮሐንስ ራዕይ በላይ ገዝፎ ህዝብህ ፍርሃት ውስጥ ይገኛል፡፡ እኛን እንዲጠብቁ የመደብካቸው ጳጳሳት፣ ፓስተሮችና ሸሆችም እኛን መጠበቅ ትተው ለራሳቸው ወጠምሻ ወጠምሻ ጠባቂ ቀጥረውልሃል፡፡ እውነት እውነት እልሃለው መቼም እውነት መሆኑን ታውቃለህ ያው ስለለመደብኝ እውነት እውነት እልሃለው አንድያ ልጅህ ክርስቶስ እንኳን አሁን ላይ ቢመጣ ስለዚህ ህዝብ ነው የሞትኩት የሚል ይመስለኛል መቼም ይህንን ከሐጢያት እንዳትቆጥረው ይመስለኛል ነው ያልኩት፡፡

ለመሆኑ አንተ የምትመጣው መቼ ነው አንተ ትመጣ ወይስ እኔ ቸኩዬ ልምጣ መልሡን አንዱ ተላላኪህ ይዞልኝ ይምጣ አንተን አላስቸግርህም፡፡ ያለሐጢያት ለመገናኘት ያብቃን፤ ደህና ልሠንብት”

ባሪያህ ይሁኔ ኤፍሬም ካሳሁን
ከኮተቤ