ልብ ብለው ያንቡት በኛ ምክንያት ብዙዎቸ በተለያየ ምክንያት ተሰናክለዋል + የአንድ ሰው ውሎና አመሻሽ + ይህ እስካሁን ምንጩን ያላገኘሁት አንድ ወንድሜ የላከልኝ በፈረንጅ አፍ የተጻፈ የቆየ የአንድ ሰው ገጠመኝ ነው :- አንድ ወንድም ስልኩን ድምፅ አልባ ማድረግ ረስቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ስብከት ይማራል:: በዚህ መካከል ስልኩ ይጮኃል:: ሰባኪው ስብከቱን አቁሞ በዓይኖቹ ተቆጣው:: ከስብከቱ በኋላ ምእመናን ስብከቱን በመረበሹ ወቀሱት:: አንዳንዶቹም እያዩት ራሳቸውን በትዝብት ነቀነቁ:: ከሚስቱ ጋር ወደ ቤታቸው ሲሔዱም ሚስቱ ስለ ቸልተኝነቱ ምክር መሥጠትዋን ቀጠለች:: እፍረት መሸማቀቅና ውርደት ዘልቆ እንደተሰማው በፊቱ ላይ ይታይ ነበር:: ከዚያች ሰንበት በኋላ እግሩን ወደ ቤተ ክርስቲያን አንሥቶ አያውቅም:: ውስጡ የተረበሸው ይህ ሰው ያንኑ ምሽት ወደ መጠጥ ቤት አመራ:: አእምሮው እንደታወከ ነበር:: ቁጭ ባለበት ድንገት የሚጠጣበት ጠርሙስ ወድቆ ተሰበረና መጠጡም በዙሪያ ተረጨ:: ፍንጣሪው የነካቸው ሰዎች ወደ እሱ መጠጋት ጀመሩ:: ሊጮኹበትና በጥፊ ሊሉት እንደሆነ ታውቆት ቀድሞ ዓይኖቹን ጨፈነ:: ሰዎቹ ግን በተሰበረው ጠርሙስ ስብርባሪ ተጎድቶ እንደሆነ ተጨንቀው ጠየቁት:: አስተናጋጁ መጥቶ የፈሰሰበትን እንዲያደርቅ ማበሻ ሰጠው:: የጽዳት ሠራተኛዋ መሬቱን ወለወለች:: የቤቱ ባለቤት "አይዞህ ያጋጥማል? ዕቃ የማይሰብር ማን አለና?" አለችውና ሌላ መጠጥ አስመጣችለት:: ከዚያች ቀን ጀምሮ ከዚያ መጠጥ ቤት ቀርቶ አያውቅም:: በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስልክን ክፍት ማድረግና ሥርዓተ አምልኮ መረበሽ መቅደስ ውስጥ ጫማ አድርጎ የመግባት ያህል ስኅተት ነው:: እንኩዋን ቤተ ክርስቲያን ኤምባሲ እንኩዋን ስልክህን ውጪ አስቀምጠህ ትገባለህ:: ሰውዬው ላጠፋው ጥፋት ግን በፍቅር የሚያናግረው ሰው በማጣቱ ከነ ስልኩ ሊጠፋ ወሰነ:: ቤተ ክርስቲያን የድኅነት ሥፍራ ናት:: መጠጥ ቤት ደግሞ የጥፋት ጎዳና ነው:: በዚህ ሰው ታሪክ ውስጥ ግን በድኅነት ሥፍራ ካሉ ሰዎች ይልቅ በጥፋት ሥፍራ ያሉ ሰዎች ለሰውዬው ስኅተት የተሻለ ፍቅር አሳዩ:: አንዳንዴ የአንዳንድ ምእመናን ጠባይ ነፍሳትን ወደ ሲኦል ይሰድዳል:: አንዳችን የአንዳችን ጠባቂ መሆን እንችላለን ዓለምን ለመፈወስ የሚቻለንን እናድርግ:: ነፍሳትን ከማዳን ነፍሳትን ማጥፋት በጣም ቀላል ነው:: መድኃኔዓለም ክርስቶስ የኃጢአተኞች ወዳጅ ነበረ:: እሱ የማንንም ቅስም በክፉ ቃል አልሰበረም:: እኛ ግን ሰው ላይ ስንጨክን መጠን የለንም:: በዚህ ምክንያት እንደ ኒቼ ያሉ ሰዎች "ብቸኛው ክርስቲያን መስቀል ላይ የሞተው ነው" ብለው እስኪዘብቱብን ደርሰዋል:: መጽሐፍ ግን ሰው ሲሳሳት ስናይ ምን ማድረግ እንዳለብን እንዲህ ሲል ይናገራል :- "ወንድሞች ሆይ፥ ሰው በማናቸውም በደል ስንኳ ቢገኝ፥ መንፈሳውያን የሆናችሁ እናንተ እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት" ገላ. 6:1 ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ የፌስቡክ ገጽ :- https://t.me/eotcy 763 viewsᵇᵉⁿᵒⁿ 🅸🅽 , 04:31