Get Mystery Box with random crypto!

#ዐይኖቼ #ታዘቡሽ በቃልኪዳን ማዕረግ ጣትሽ ከጣቴ ጋር በህግ ተሳስሮ፡ ሀገር መስክሮልን ሁለትነት | እንደመሠለን🥴😂❤️

#ዐይኖቼ #ታዘቡሽ

በቃልኪዳን ማዕረግ ጣትሽ ከጣቴ ጋር በህግ ተሳስሮ፡
ሀገር መስክሮልን ሁለትነት የለም አንድ ናቸው ብሎ፡
ተሳስረን ነበረ ዘመን ልንገፋበት፡
መፃሂውን ህይወት፡
ምልክት ባለበት በሀቲብ ቀለበት፡
በውቢቷ ሣራ በነ አብረሃም ወግ፡
ዳግም በማይፈታ በህቡዐተ ክር በጠንካራ ሀረግ፡:

ግና ውዴ ዛሬ አየኋቸው ሁሉንም አካላቶችሽን በትኩረት አማተርኩ፡
የተገላቢጦሽ ስታዘብ የኖርኩት ዛሬ እኔ አንቺን ታዘብኩ፡፡

ፍቅሬ፡ ያሁሉ ምሀላ ፍቅራችን ቀረና፡
ዳግመኛ ላንጓዝ አብረን ላንራመድ በህይወት ጎዳና፡
በስምሽ እንዳልማልኩ በስሜ እንዳልማልሽ፡
እንዳልተገዘትን መቼም ለንቷቷው መቼም ላንወሻሽ፡
በሐቅ ተመስርተን፡
ፍሰቱ እንዲጨምር መውደዳችን በዝቶ እንዲሆን እልፍ አእላፍ፡
ይቅርታን ልናሰርጽ ትዕግስትን ልናተርፍ፡፡

ተማምለን ነበር በልብ ተደጋግፈን የብቸኝነትን ተራራ ልናፈርስ፡
ከሣቅኩኝ ልትስቂ ካለቀሽ ላለቅስ፡፡

ዛሬ ላይ ግን ውዴ ሁሉን አሳየሽኝ ሁሉንም ተአምር ፡
ከጥፍርሽ አንስተሽ እስከ ራስሽ ጠጉር፡፡

ሆዴ፡ እኒያ ኮከብ ዐይኖች ከፊትሽ ላይ ያሉት፡
በጠራው ገፅሽ ላይ የሚንከባለሉት፡
ያኔ ሳንለያይ ልክ እንደ ጨቅላ ልጅ የምሳሳላቸው እንዲያ ምወዳቸው፡
ዛሬ ግን አስከፉኝ ውስጤ አዘነባቸው፡፡

ያኔ ስንማማል በጥብቁ ማህተቤ በጥብቁ ማህተብሽ፡
እጅሽ እጄን መቶ አንቺነትሽ አንቺን ለኔ ሲያስረክብሽ፡፡

ጥቁር ብሌኖችሽ ከዐይኔ ጋር ተፋጠው፡
አጣማሪ ሳይሹ በአንዳች መግነጢስ በቅፅበት ተግባብተው ፡
በጥብቅ ተሳስበው ውስጥሽና ውስጤ በአንዳች ተዓምር ፡
ሌላውን ላያዩ ዐይንሽ ከዐይኖቼ ጋር ተማምለው ነበር፡፡

በርግጥ ሁሉም አልፎ የሆነውም ሁኗል፡
ዳግመኛ አንድ እንዳንሆን ውስጥሽና ውስጤ አንዴ ተቃቅሯል፡
ያብራ ግዜአችን የአበባው ዘመን ከአድማሱ ተሻግሮ ትዝታ ሁኖ ቀርቷል፡
የትናንት ኑሮአችን ፍቅራችን ተረስቶ ታሪክ ሁኖ አልፏል፡
እንደ ፈሰሰ ውሃ እንደ አልቦ ነገር ባዶ ሁኖ ባክኗል፡፡

እናልሽ ፀዳሌ የትናንቱ መሀላ በዛሬ ተረስቶ፡
የዐይንሽና የዐይኔ እስራቸው ተፈቶ ቃላቸውም ቀርቶ፡
አንቺም እኔን ተውሽኝ ልቤም ቆረጠልሽ፡
ዐይኖችሽን ከዐይን ላይመለሱ አንስተሽ፡
ወደ ሌላ ስትሄጅ እኔን ማየት ትተሽ፡
አዘንኩብሽ ውዴ ዐይኖቼ ታዘቡሽ፡፡

2013 ዓ.ም
ፍራኦል አብዲሳ (ዝምተኛው ኮብላይ)