Get Mystery Box with random crypto!

እስከ 40 ሺሕ የሚደርሱ የአማራ ተወላጆች ተገድለዋል ተባለ =======#======= በኢትዮጵ | EMS Mereja

እስከ 40 ሺሕ የሚደርሱ የአማራ ተወላጆች ተገድለዋል ተባለ
=======#=======

በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ ከተደረገበት 2010 ወዲህ ባሉት ዓመታት ከ25 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ የሚገመቱ የአማራ ተወላጆች በአክራሪ ብሔርተኞች መገደላቸውን ካውንተር ፓንች በድህረ ገጹ አስነብቧል።

ዘገባው አብዛኞቹ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚል በሚጠራው እና በመንግሥት “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ በተፈረጀው ኃይል የተገደሉ መሆናቸውን መገለጹን አዲስ ማለዳ ከድህረ ገጹ ዘገባ ተመልክታለች፡፡

ከዚህ ባለፈም፤ ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች በየጊዜው በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸው ነው የተገለጸው።

እንዲሁም በአገሪቱ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከጊዜ ወደ ጊዜ አደጋ ውስጥ እየገባ ነው የተባለ ሲሆን፤ የመሰበሰብ፣ የሚዲያ ነጻነት እና ሌሎች ተያያዥ ዴሞክራሲያዊ መብቶች አደጋ ውስጥ መግባታቸው ተጠቅሷል።

በዚህም ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ የአገር ውስጥ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ በግልጽ የሚናገሩ ጋዜጠኞች እና የግል የሚዲያ ተቋማት በነጻነት የመናገርና የመስራት መብታቸውን አጥተዋል ሲል የካውንተር ፓንች ዘገባ አመላክቷል።

ዘገባው መሰረቱን በአሜሪካ ያደረገ “ፍሪደም ሃውስ” የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅትን መረጃ ጠቅሶ፤ በኢትዮጵያ በስፋት መንግሥትን የሚተቹ አካላት ከእውቅናቸው ውጭ በሆነ መንገድ በመንግሥት የደህንነት አካላት በእጅ ስልካቸው ላይ ሳይቀር ሚስጥራዊ ክትትል እንደሚደረግባቸው ጠቁሟል።

በአገሪቱ የዘፈቀደ እስራት በተደጋጋሚ እንደሚፈጸም በመጥቀስም፤ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ አክቲቪስቶች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሠራተኞች ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሥራ ቦታቸው ወይም ከመንገድ ላይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በደህንነቶች ተይዘው ወዳልታወቀ ቦታ እንደሚወሰዱምተገልጿል።

በአገሪቱ ሥር የሰደደ ሙስና መኖሩን የጠቀሰው ዘገባው፤ ገንዝብ ተቀብለው ፍርድ የሚያጣምሙ ዳኞች ላይ ሳይቀር ያለው ተጠያቂነትም እምብዛም ነው ብሏል።

የጋዜጠኞች መብት ተማጋች ሲፒጄ በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች ነጻነት አሳፋሪ ገጽታ እንዳለው በመጠቆም፤ ባለስልጣናት የታሰሩትን ጋዜጠኞች በሙሉ ሊለቁ እንደሚገባና እስር ቤት ውስጥ በነበሩበት ወቅት በደል ወይም ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል የሚለውን መመርመር ብሎም ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባቸው ማሳሰቡ ይታወሳል።

አብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ ትልቅ ተስፋ ጥሎበት የነበረው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር፣ ቀስ በቀስ ራሱን ወደ አምባገነናዊ ስርዓት እየለወጠ ነው ሲልም ካውንተር ፓንች በዘገባው አመላክቷል።
ሼር አድርጉት
ለትክክለኛ ወቅታዊ መረጃዎች ቻናላችንን join በማድረግ ተከታተሉ
http://t.me/emsmereja