Get Mystery Box with random crypto!

ሰኞ ምሽት! ሰኔ 26/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች 1፤ ኢሠማኮ መንግሥት የሠራተኞችን ዝ | EMS Mereja

ሰኞ ምሽት! ሰኔ 26/2015 ዓ.ም የEMS ዐበይት ዜናዎች

1፤ ኢሠማኮ መንግሥት የሠራተኞችን ዝቅተኛ ደመወዝ የሚወስን የደመወዝ ቦርድ ባለማቋቋሙ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፍትሄ እንዲሰጠው ጥያቄውን ማቅረቡን መግለጡን ሪፖርተር ዘግቧል። የሥራና ክህሎት ሚንስቴር በበኩሉ፣ የደመወዝ ቦርድ ጉዳይ ጥናት እየተደረገበት እንደኾነ መናገሩን ዘገባው ጠቅሷል። የሥራና አሠሪ አዋጅ መንግሥት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን የሚወስን የደመወዝ ቦርድ እንዲቋቋም ደንግጓል።

2፤ በጋምቤላ ክልል አኝዋክ ብሄረሰብ ዞን ዲማ ወረዳ በታጣቂዎች ተኩስ ሁለት ጸጥታ በማስከበር ሥራ ላይ የነበሩ የመንግሥት ጸጥታ ኃይል አባላት እንደተገደሉ ዶይቸቨለ ዘግቧል። ታጣቂዎቹ አንድ ሌላ የክልሉ መንግሥት ሚሊሺያ አባልን ማቁሰላቸውን የዲማ ወረዳ አስተዳደር ኮምንኬሽን ቢሮ መናገሩን ዘገባው ጠቅሷል። የታጣቂዎቹን ማንነት ዘገባው አልጠቀሰም። በክልሉ ይንቀሳቀስ የነበረው አማጺ ቡድን፣ በቅርብ ወራት ከመንግሥት ጋር እርቅ ፈጽሞ ወደ ሰላማዊ ኑሮ መመለሱ እንደተገለጠ ይታወሳል።

3፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ "ቦይንግ- 787-9" የተሰኘውን 10ኛውን ድሪም ላይነር አውሮፕላኑን መረከቡን አስታውቋል። አውሮፕላኑ ባለፈው ሳምንት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ማረፉንና የመጀመሪያ በረራውን ከአዲስ አበባና ወደ ዱባይ ማድረጉን አየር መንገዱ ገልጧል።

4፤ በቻይና ብድር የተገነባው. የኢትዮጵያ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ባለፉት አምስት ዓመታት 1 ሺህ 824 ጊዜ የመንገደኞች ማመላለሻ ባቡሮች እንደተመላለሱበት የትራንስፖርት ሚንስትሩ ዓለሙ ስሜ መናገራቸውን ጠቅሶ ዥንዋ ዘግቧል። የባቡሩ ትራንስፖርቱ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 530 ሺህ 900 መንገደኞችን በ6 ሺህ 133 የካርጎ ባቡር ምልልሶች ከ7 ሚሊዮን 328 ሺህ ቶን በላይ ሸቀጦችን ማጓጓዙን ሚንስትሩ መግለጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል። ዓለሙ ይህን የተናገሩት፣ በኢትዮጵያና ቻይና የቤልት ሮድ ፕሮጀክት ዙሪያ በተደረገ የጋራ ውይይት ላይ እንደኾነ ተገልጧል።

5፤ በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን አማኑኤል ከተማ ነዋሪ የኾኑ አንለይ መኩሪያ የተባሉ ጡረተኛ መምህር ልጃቸውን በ1 ሚሊዮን ብር ክፍያ ከእገታ አስለቅቄያለኹ ማለታቸውን ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል። የመምህሩ ልጅ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሰኔ 10 ቀን ከታገቱት 30 ሹፌሮችና ረዳቶቻቸው አንዱ እንደነበር ዘገባው አመልክቷል። የታጋቹ ወላጅ አባት የልጃቸውን ማስለቀቂያ ገንዘብ ያሰባሰቡት ከጎረቤቶቻቸውና ከዘመድ አዝማድ እንደኾነ ዘገባው ጨምሮ ጠቅሷል። መምህሩ 1 ሚሊዮን ብሩን ለአጋቾቹ ያስረከቡት፣ ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገብረጉራቻ ከተማ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደኾነ ተገልጧል።

6፤ ንግድ ባንክ ዛሬ የአንድ ዶላር መግዣ ዋጋ 54 ብር ከ6052 ሳንቲም እና መሸጫ ዋጋው 55 ብር ከ6973 ሳንቲም ሆኖ እንደዋለ በድረገጹ ገልጧል። የአንድ የእንግሊዝ ፓውንድ መግዣ ዋጋ ደሞ 66 ብር ከ1810 ሳንቲምና መሸጫው 67 ብር ከ5046 ሳንቲም ሆኗል። በተመሳሳይ አንድ ዩሮ በ59 ከ5524 ሳንቲም ተገዝቶ፣ በ60 ብር ከ7434 ሳንቲም ሲሸጥ መዋሉን ባንኩ ገልጧል።
ሼር ይደረግ


ለትክክለኛ ወቅታዊ መረጃዎች ቻናላችንን join በማድረግ ተከታተሉ
http://t.me/emsmereja