Get Mystery Box with random crypto!

ከጦርነትና የሰላም ስምምነት በኋላ ህይወት በትግራይ ምን ይመስላል? የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ተ | EMS Mereja

ከጦርነትና የሰላም ስምምነት በኋላ ህይወት በትግራይ ምን ይመስላል?

የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ተስፋቸውን እና ስጋታቸውን ነግረውናል


ከጦርነትና የሰላም ስምምነት በኋላ ህይወት በትግራይ ምን ይመስላል?

የትግራይ ክልል ነዋሪዎች ተስፋቸውን እና ስጋታቸውን ነግረውናል

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት እንዲቆም ምክንያት የሆነው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ስድስት ወር አልፎታል

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ በሕወሃት ታጣቂዎች መጠቃቱን ተከትሎ ነበር በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተጀመረው።

ለሁለት ዓመት ገደማ በተካሄደው በዚህ ጦርነት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ህይወታቸውን ሲያጡ የ28 ቢሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ውድመትም አድርሷል።

የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ሀይሎች በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ጦርነቱ ቆሟል።

የሰላም ስምምነቱን ተከትሎም በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር የተቋቋመ ሲሆን መንግስታዊ አገልግሎቶች ዳግም ወደ ስራ ተመልሰዋል።

አል ዐይን አማርኛ በትግራይ ከሰላም ስምምነቱ እና ከጊዜያዊ አስተዳድር መመስረት በኋላ ህይወት እንዴት እየቀጠለ ነው ሲል በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

በክልሉ መዲና መቐለ ነዋሪ የሆነው አብርሃ ሀይለማርያም እንደነገረን ከሆነ በከተማዋ የሰላም ስምምነት በተፈረመበት ጊዜ ህዝቡ ፍጹም ደስታ ተሰምቶት እንደነበር ነግሮናል።

አሁንም ቢሆን እኔን ጨምሮ የከተማዋ ነዋሪ ለሰላም ስምምነቱ ትልቅ አክብሮት አለው የሚለን አብርሃ ስምምነቱ ግን የጠበቅነውን ያህል እየተፈጸመ እንዳልሆነ እንረዳለን ብሎናል፡፡

በከተማዋ የክልሉ እና የፌደራል መንግስት ተቋማት ወደ አገልግሎት መመለሳቸውን ተከትሎ የነበረው አስከፊ ዝርፊያ፣ የመንቀሳቀስ ነጻነት እና የኑሮ ውድነቱ መሻሻል ማሳየቱን አብርሃ አክሏል፡፡

አንድ ኩንታል ጤፍ እስከ 20 ሺህ ብር ድረስ ይሸጥ ነበር አሁን ግን ከ8 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር በመሸጥ ላይ ነው፣ ሌሎች ምርቶችም ከክልሉ ቦታዎችም ሆነ ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ገበያ እየቀረቡ ነውም ብሏል፡፡

ይሁንና በከተማዋ ከባንኮች ውጪ ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሟላ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን፣ አሁንም በከተማዋ ምሽት ላይ ዝርፊያ መኖሩ፣ የሰላም ስምምነቱ በሙሉ ላይተገበር ይችላል፣ በየትምህርት ቤቶቹ ያሉ ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው አለመመለስ እና እርዳታ የሚፈልገው ህዝብ መብዛት በከተማዋ ያለ ዋነኛ ችግር እንደሆነ አብርሃ አክሏል፡፡

ለደህንነቱ ሲል ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ እና የአዲግራት ከተማ ነዋሪ አስተያየት ሰጪ እንዳለው ከሆነ በከተማዋ እና በአካባቢው ባሉ የወረዳ ከተሞች አሁንም ከመልካም ነገሮች ይልቅ ስጋቶች እና ችግሮች እንደሚብሱ ነግሮናል፡፡

አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ከመቀበል ይልቅ የኤርትራ ጦር ከያዛቸው አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች መኖሪያ ሆነዋል የሚለን ይህ የአዲግራት ከተማ ነዋሪ ምሽት ላይ ዘረፋ መኖሩን፣ እርዳታ የማይሰጡ ነገር ግን ለአይን የሚታክቱ የረድኤት ድርጅቶች እንቅስቃሴ መኖሩን እንዲሁም አገልግሎት የማይሰጡ የመንግስት ተቋማት መኖራቸውንም አክሏል፡፡

አስተያየት ሰጪው አክሎም የረድኤት ድርጅቶች ለተረጂዎች ምግብ እና ቁሳቁስ እየጫኑ ወደ ከተማዋ እና ወረዳዎች ሲሄዱ ብናይም የሚረዱት ግን ጥቂቶች ብቻ መሆናቸውን ነግሮናል፡፡

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳድር ተዋቅሯል ሲባል መስማቱን የነገረን ይህ አስተያየት ሰጪ ነገር ግን የመንግስት ተቋማት አገልግሎት መስጫዎች በጦርነቱ ስለወደሙ እና ስለተዘረፉ አገልግሎት መስጠት አልቻሉም ብሏል፡፡

በአዲግራት አካባቢ ያለው ህዝብም አብዛኛወው እርዳታ ጠባቂ ነው ያለን ይህ ነዋሪ ህዝቡ ውጪ ሀገራት እና በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ካሉ ቤተሰቦቹ በሚላክለት ገንዘብ እንደሆነም አክሏል፡፡

በተጨማሪም ልጆቻቸውን ወደ ጦርነቱ የላኩ ቤተሰቦችም የልጆቻቸውን ሁኔታ ባለማወቃቸው አልያም ከዛሬ ነገ መርዶ ይመጣል በሚል ስጋት ውስጥ ያሉ ሰዎችም ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ይሄው ነዋሪ ነግሮናል፡፡

የኤርትራ ጦር አሁንም ዛላምበሳ እና አካባቢው ካሉ አካባቢዎች ካለመውጣቱ ባለፈ የተወሰኑ ቀበሌዎች ውስጥ ያሉ መኖሪያ ቤቶችን እና የሕዝብ ተቋማትን በማፍረስ ላይ መሆኑ የአካባቢውን ህዝብ እንዳሳሰበ ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኤርትራ ጦር ከዚህ በፊት ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦርነት መጀመር ምክንያት ከሆነው ከባድመ ውጪ የሆኑ የኢትዮጵያ እና ትግራይ ክልል ግዛት ስር የነበሩ ቀበሌዎችን እንደ ራሱ አድርጎ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ላይ መሆኑን ይሄው ነዋሪ ነግሮናል፡፡

ይህን ተከትሎም ህዝቡ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ዳግም ጦርነት ልንገባ እንችላለን የሚል ስጋት ውስጥ መውደቁን ነዋሪው ገልጿል፡፡

ሌላኛው የአክሱም ከተማ ነዋሪ የሖነው እና ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አስተያየት ሰጪ በበኩሉ የሰላም ስምምነቱ ለህዝቡ ትልቅ እፎይታን እንዳመጣለት ነግር ግን መሻሻል ያለባቸውን ጉዳዮች እንዳሉ ዘርዝሯል፡፡

በአክሱም እና አጎራባች አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች በግማሽ መከፈታቸውን የነገረን ይህ ነዋሪ ትምህርት ቤቶች የተፈናቃዮች መኖሪያ መሆናቸው እና የጦርነቱ ውስብስብ ጠባሳዎች የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት እንደጎዳው ነግሮናል፡፡
ከመንግስት ትምህርት ቤቶች ይልቅ የግል ትምህርት ቤቶች የተሻለ ተማሪ ቁጥር አላቸው ያለን ይህ አስተያየት ሰጪ የመሬት ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ችግር አለመፈታት ዋነኛ የአካባቢው ህዝብ ስጋት መሆኑን አክሏል፡፡

የኤርትራ ጦር ከክልሉ ይዞታዎች አሁንም አለመውጣቱ፣ የኢኮኖሚው ችግር አለመፈታት፣ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ አለመከፈል እና ለተፈናቃዮች እርዳታ እየተሰጠ አለመሆኑ ሌላኛው የአክሱም እና አካባቢው ህዝብ ችግሮች ናቸውም ተብሏል፡፡

የረድኤት ድርጅቶች 10 ቤተሰብ ላለው ተረጂ የሶስት ሰው መስጠት ሶስት ቤተሰብ ላለው ደግሞ ለ10 ሰው የሚበቃ እርዳታ ሲሰጡ አያለሁ የሚለን ይህ አስተያየት ሰጪ ወደ አካባቢው እየተጓጓዘ ያለው የእርዳታ መጠን ከፍተኛ ቢሆንም እየተሰጠ ያለው እርዳታ ግን አነስተኛ መሆኑንም ነግሮናል፡፡

የሰላም ስምምነት በመፈረሙ ደስተኞች ነን የሚለው ይህ ነዋሪ አርሶ አደሮች ወደ እርሻቸው፣ ሌላውም ማህበረሰብ ወደ ለመደው የቀድሞ ህይወት በቶሎ እንደሚመለስ ተስፋ አድርገን ነበር ነገር ግን የሰላም ስምምነቱ የታሰበውን ያህል እየተፈጸመ አለመሆኑ ህዝቡ አሁንም ዳግም ወደ ጦርነት እንገባ ይሆን የሚል ስጋት አለውም ብሎናል፡፡

ህይወቴን በትምህርት ቤት በረንዳዎች ላይ ካደረግሁ ሶስተኛ ዓመቴ ሊመጣ ነው ያለችን ሌላኛዋ የሽሬ ከተማ ነዋሪ ነች፡፡

ሶስት ልጆቿን ይዛ ከአማራ ክልል አዋሳኝ ቀበሌ እንደተፈናቀለች የነገረችን ይቺ ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች አስተያየት ሰጪ ከዛሬ ነገ ወደ ቤቴ እመለሳለሁ ብልም እስካሁን እንዳልተሳካላት ነግራናለች፡፡

የሰላም ስምምነት ተፈረመ ስንባል በደስታ እልል ብለናል የምትለው ይህች አስተያየት ሰጪ በፊት እርዳታ ጥሩ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ቆሟል አልፎ አልፎ ትንሽ ትንሽ ይሰጡናል ብላናለች፡፡